በደቡብ ወሎና በምስራቅ ጎጃም ዞኖች 431 ሚሊዮን ችግኝ ለተከላ ተዘጋጀ

136

ደሴ/ ደብረ ማርቆስ (ኢዜአ) ግንቦት 15 /2012  በደቡብ ወሎና ምስራቅ ጎጃም ዞኖች በዘንድሮው ክረምት የሚተከል 431 ሚሊዮን ችግኝ መዘጋጀቱን የየዞኖቹ ግብርና መምሪያዎች አስታወቁ።

የደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ አሊ ሰይድ ለኢዜአ እንደገለጹት በዚህ ዓመት 191 ሚሊዮን ችግኝ በተራቆት መሬት ላይ ለመትከል ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡

ለዚሁ ተግባር የሚውል 42 ዓይነት አገር በቀልና የውጭ ዝርያ ያላቸው ችግኞች በ18 ሺህ ችግኝ ጣቢያዎች ተፈልቶ መዘጋጀቱን ጠቅሰዋል።

በሚተከለው ችግኝ 42 ሺህ ሄክታር መሬት ለመሸፈን መታሰቡን ጠቅሰው 34 ሚሊዮን የመትከያ ጉድጓድ ተቆፍሮ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

ችግኞችን መትከል ብቻ ሳይሆን የመጽደቅ መጠኑ እንዲጨምርም ከወዲሁ በጥንቃቄ እየተሰራ ይገኛል።

የሚተከሉ ችግኞች የአየር ሚዛንን ለመጠበቅ፣ በረሃማነትን ለመከላከል፣ የአፈር ለምነትን ለማሻሻል ጠቀሜታ ያላቸው መሆኑን በመገንዘብ ህብረተሰቡ በየአካባቢው ችግኝ በመትከል የድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡

በደሴ ዙሪያ ወረዳ የ020 ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ሽመልስ አህመድ በበኩላቸው ምርት በማይሰጥ ማሳቸው ላይ ከሦስት ሺህ በላይ የባህር ዛፍና ጽድ ችግኝ ለመትከል ቅድመ ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ባለፈው ዓመት የተከሉት ከአንድ ሺህ በላይ ችግኝ ከግብርና ባለሙያዎች ባገኙት ምክርና ድጋፍ ተንከባክበው አብዛኛው እንደጸደቀላቸው ገልጸዋል፡፡

በቃሉ ወረዳ የሀርቡ ከተማ ነዋሪ ወጣት መሃመድ ሲራጅ በበኩሉ በየዓመቱ የአትክልትና ፍራፍሬ ችግኝ እያፈላ ተጠቃሚ መሆኑን ገልጿል፡፡

ዘንድሮም 2ሺህ 500 የማንጎና ብርቱካን ችግኝ እያዘጋጀ ሲሆን ከ100 ሺህ ብር በላይ ለመሸጥ አቅዶ እየሰራ መሆኑን ተናግሯል፡፡

በደቡብ ወሎ ዞን ባለፈው ክረምት ከተተከለው 216 ሚሊዮን ችግኝ ውስጥ ከ81 በመቶ በላይ መጽደቁ በቆጠራ መረጋገጡን ከመምሪያው የተገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

በተመሳሳይ በምስራቅ ጎጃም ዞን የደን ሽፋኑን ለማሻሻል በዚህ የክረምት ወቅት 241 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል የቦታ መረጣ ስራ መከናወኑን የዞኑ ግብርና ማምሪያ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ቡድን መሪ አቶ ንጉሴ ሽመልስ ገልፀዋል ።

ችግኖቹ የሚተከሉት በ56 ሺህ ሄክታር የወል፣ የግለሰብ፣ የድርጅት ቦታዎችና በበጋው ወራት የአፈር እና ውሃ ጥበቃ ስራ በተከናወነባቸው አካበቢዎች ላይ መሆኑን አስረድተዋል።

ከሚተከሉት ችግኞች መካከልም ዋንዛ፣ ወይራ፣ሰሳ፣ ኮሶ፣ የአበሻ ጽድ፣ ብሳና፣ ግራቭሊያ፥ ሳስፓኒያ፥ ዲከረስ የመሳሰሉት ይገኙበታል

ባለፈው አመት ከተተከለ ችግኝ ውስጥም በተደረገው እንክብካቤና ጥበቃ ከ70 በመቶ በላይ የጸደቀ መሆኑን ያስረዱት አቶ ንጉሴ ለዚህም የማህበረሰቡ የባለቤትነት ስሜት አስተዋጽኦ እንዳበረከተ ጠቁመዋል።

 የአዋበል ወረዳ የእነብይ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ይግዘው ላቀ እንዳሉት "በየአመቱ በጋራም ሆነ በግል ማሳችን የሚተከሉ ችግኖች አፈራችን በጎርፍ እና በነፋስ እንዳይሸረሸር እገዛ እያደረገልን" ነው።

ችግኝ እንደ ልጅ ነው በማለት በየወቅቱ ውሃ ማጠጣት፣ መኮትኮትና ከእንስሳት ንክኪ በመጠበቅ የተተከሉ ችግኞችን እየተንከባከቡ መሆናቸውን የገለፁት ደግሞ የጎዛምን ወረዳ የአባ ሊባኖስ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ደረበ መክት ናቸው።

በቀጣይም የተከላም ሆነ የእንክብካቤ ስራቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቅሰው በዚህ ክረምት ወቅት በግል ጓሮአቸው የሚተክሉ 100 እግር የጌሾ ችግኝ ማዘጋጀታቸውን አመልክተዋል።

በምስራቅ ጎጃም ዞን ከ284 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በደን የተሸፈነ እንደሆነም ከመምሪያው የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም