በባለሃብቶች ተይዘው የማይለሙ መሬቶች ወደ ሥራ መግባት አለባቸው-ተወካዮች ምክር ቤት

3715

አዲስ አበባ ግንቦት 1/2010 የሆርቲካልቸርና ግብርና ኢንቨስትመንት ባለሥልጣን በባለሃብቶች የተያዙ መሬቶች ወደ ሥራ እንዲገቡ መሥራት እንዳለበት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ።

የምክር ቤቱ የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የባለሥልጣኑን የዘጠኝ ወራት እቅድ አፈጻጸም ዛሬ ገምግሟል።

ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ ያዕቆብ ያላ ሪፖርቱን ሲያቀርቡ እንዳሉት፤ በበጀት ዓመቱ ከሆርቲካልቸር ዘርፍ 328 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ ነበር።

በእቅድ ከተያዘው ባነሰ 224 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን የገለጹት ሥራ አስፈጻሚው ይህም የአፈጻጸሙ 68 በመቶ መሆኑን አንስተዋል።

ገቢው የተገኘው ከጽጌረዳ አበባ፣ እንቡጥ አበባና አትክልትና ፍራፍሬ ሲሆን ከእቅዱ ጋር ሲነጻጸር ገቢው ዝቅተኛ መሆኑን ነው ዋና ሥራ አስፈጻሚው ያብራሩት።

የአውሮፓ ማዕከላዊ ገበያ መውረዱ፣ በአገሪቷ ተከስቶ የነበረው አለመረጋጋትና አንዳንድ ኩባንያዎች በሙሉ አቅማቸው ወደ ሥራ አለመግባታቸው ለአፈጻጸሙ ዝቅተኛ መሆን በምክንያትነት ተቀምጠዋል።

የቋሚ ኮሚቴው አባላት በበኩላቸው ለባለሃብቶች መሬት የሚሰጥበት መስፈርት ምንድነው? ባለሀብቶች መሬትን ወስደው ያለማልማት፣ በከፊል የማልማት እንዲሁም ከተፈቀደላቸው ውጪ ሥራዎች ሲሰሩ ይታያል እዚህ ላይ ምን እየተሰራ ነው? ሲሉ ጠይቀዋል።

አቶ ያዕቆብ በሰጡት ምላሽ “መሬት ወስደው ወደ ልማት ላልገቡ ባለሃብቶች ከማስጠንቀቂያ ጀምሮ ውል የማቋረጥ እርምጃዎች እየተወሰዱ ናቸው” ብለዋል።

ለአብነትም ሩቺ የተሰኘው ኩባንያ 10 ሺህ ሄክታር መሬት ለማልማት ውል ቢገባም  ማልማት የቻለው 3 ሺህ ሄክታር ብቻ በመሆኑ በህጉ መሰረት ውሉ እንዲቋረጥ መደረጉን ተናግረዋል።

በተመሳሳይም ካራቱሪ የሚባል ኩባንያም በውሉ መሰረት መስራት ባለመቻሉ ያላለማውን መሬት እንዲመለስ የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሆነ አስረድተዋል።

ባለሃብቶች ወደ ሥራ እንዳይገቡ ከሚያደርጋቸው ጉዳዮች መካከል የመሰረተ ልማት አቅርቦት ችግር ዋነኛው መሆኑን የገለጹት አቶ ያዕቆብ፤ ባለሥልጣኑ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የመሰረተ ልማት አቅርቦት ላይ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ አልማዝ መለሰ እንደገለጹት ባለሥልጣኑ በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት አዳዲስ የአሰራር መመሪያዎችን ማውጣቱ በጠንካራ ጎን የሚታይ ነው።

ከመሰረተ ልማት አቅርቦትና ከጸጥታ መደፍረስ ጋር በተያያዘ የሚስተዋሉ ችግሮችን ባለሥልጣኑ ለመፍታት የጀመራቸው እንቅስቃሴዎች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው ብለዋል።

በተለይ የሆርቲካልቸር ምርቶች ገቢ አፈጻጸም አነስተኛ መሆኑ መሻሻል እንዳለበት ያሳሰቡት ሰብሳቢዋ ችግሩን ለማቃለል አዳዲስ የገበያ መዳረሻዎችን ማስፋት ላይ በትኩረት መሰራት አለበት ብለዋል።

መሬቱ በአግባቡ እንዲለማና የኀብረተሰቡ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ የአካባቢ ጥበቃ ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባም ወይዘሮ አልማዝ አጽንኦት ሰጥተዋል።