በአፋር ክልል ከ200 በላይ ታጣቂ ኃይሎች ወደ ሰላማዊ ሕይወት ተመለሱ

57

አፋር፣ ግንቦት 14/2012 (ኢዜአ) በአፋር ክልል በሕገ ወጥ መንገድ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ከ200 በላይ ታጣቂ ኃይሎች የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎትና የአገር መከላከያ ሠራዊት ባደረጉት ጥረት ወደ ሰላማዊ ህይወት ተመለሱ፡፡

በአገሪቱ የተጀመረው የሰላም አማራጭ በቀጣይ ለአገር ሰላምና ደህንነት ግንባታ አስተዋጽኦ ለማበርከት እንደሚያስችላቸው ታጣቂዎቹ ተናግረዋል፡፡

ከሁለት ዓመታት በፊት የተፈጠረውን አገራዊ ለውጥ ተከትሎ የትጥቅ ትግል ለሚያደርጉ ኃይሎች የሰላም ጥሪ መተላለፉ ይታወሳል።

በዚህ መሠረት በኤርትራ ቆላማ አካባቢዎች ከሁለት አሥርት አመታት በላይ ሲንቀሳቀስ የነበረው የአፋር አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ግንባር (እጉጉሞ) ከ300 በላይ ታጣቂ ኃይሎች ባለፈው ዓመት ሰላማዊ ትግልን መርጠው ወደ አገራቸው መግባታቸው አይዘነጋም፡፡

ሰላማዊና ህጋዊ መንገድን መርጠው ወደ አገር ውስጥ ገብተው ከነበሩት የታጣቂ ቡድኑ አባላት የተወሰኑት በመካከላቸው በተፈጠረ አለመግባባት ከማቆያ ካምፕ በመውጣት እንደገና ወደ ቀድሞ የታጣቂነት ሕይወታቸው ተመልሰዋል፡፡

ይህን መነሻ በማድረግም ብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ከኢፌዴሪ አገር መከላከያ ሠራዊት ጋር በመሆን የአገርንና የህዝብን ሰላምና ደህንነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ በማለም ታጣቂዎቹ በተሰማሩባቸው አካባቢዎች በጥብቅ ሙያዊ ምስጢርና ሥነ ምግባር መረጃ ሲያሰባስቡ ቆይተዋል፡፡

ይህን ተከትሎም ከ35 ዲግሪ እስክ 43 ዲግሪ ሴልሺየስ ሞቃታማ የአየር ሁኔታ በሚስተዋልበት፤መልክዓ ምድራዊ አቀማመጡም በአብዛኛው ተራራማና ድንጋያማ በሆነባቸው ቆላማ አካባቢዎች የነበሩ ታጣቂ ኃይሎች ከአፋር ክልል መንግሥት፤ከአገር ሽማግሌዎችና ከጎሳ መሪዎች ጋር ተከታታይ ውይይት አድርገዋል፡፡

በመሆኑም እነዚህ ኃይሎች በቀጣይ ከነፍጥ ይልቅ ሰላማዊ መንገድን አማራጭ አድርገው እንደሚንቀሳቀሱ አረጋግጠዋል፡፡

ከክልሉ መንግሥትና ከኅብረተሰቡ ጋር ሆነው በቀጣይ በክልሉ እንዲሁም በአገር ሰላምና ደህንነት ግንባታ ረገድ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅትም ታጣቂ ኃይሎቹ የተሃድሶና የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናዎችን ወስደው፤ በሰላም ሚኒስቴርና በክልሉ መንግሥት የገንዘብ ድጋፍ ተደርጎላቸው በቀጣይ ሰላማዊ ሕይወታቸውን ለመምራት ከማህበረሰቡ ጋር እንዲቀላቀሉ ተደርጓል፡፡

የገንዘብ ድጋፍ ተደርጎላቸው ወደ ሰላማዊ ሕይወት የተቀላቀሉት ባለፈው ዓመት የገቡትን ጨምሮ ከ500 በላይ መሆናቸውን መረጃው ይጠቁማል፡፡

ብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎትና የኢፌዴሪ አገር መከላከያ ሠራዊት ለሰላም ሂደቱ ስኬት ከፍተኛ ድጋፍ ላደረጉት ለአፋር ክልል የአገር ሽማግሌዎችና ለጎሳ መሪዎች ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በመጨረሻም 1 ሺህ 441ኛውን የኢድ አልፈጥር በዓልን ምክንያት በማድረግ በጋራ ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ሕዝበ ሙስሊሙም ሆነ መላው የአገራችን ሕዝቦች የኮቪድ 19ኝ ወረርሽኝ ለመከላከል የጀመሩትን ሁለንተናዊ ጥረት አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል፡፡

ከበዓሉ አከባበር ጋር በተያያዘ ማንኛውም አካል ለአገር ሰላምና ደህንነት ስጋት የሆነ የተለየ እንቅስቃሴ ሲመለከት በአካባቢው ለሚገኙ የፀጥታ አካላት ጥቆማ በመስጠት የተለመደ ትብብሩን እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም