ግብጽ የአስዋንን ግድብ ስትገነባ የኢትዮጵያን ፈቃድ አልጠየቀችም - የመብቶች ተሟጋች ጄሲ ጃክሰን

138

አዲስ አበባ   ግንቦት  13/2012 (ኢዜአ) "ግብጽ የአስዋንን ግድብ ስትገነባ የኢትዮጵያን ፈቃድ አልጠየቀችም" ሲል ጥቁር አሜሪካዊው የመብቶች ተሟጋች ጄሲ ጃክሰን አስታወቁ። ኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድቡን አስመልክቶ የምታከናውናቸው ስራዎች ዓለም አቀፍ የውሃ ህጎችን የተከተለ ነውም ብለዋል።

የሲቪክ መብቶች ተቋም "ሬንቦው ፑሽ ኮሊሽን" መስራች ጄሲ ጃክሰን ለጥቁር የአሜሪካ ኮንግረስ አባላት ኮሚቴ ሊቀመንበር ሚስ ካረን ባስ በጻፉት አራት ገጽ ደብዳቤ ላይ እንዳሰፈሩት ግብጽ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ያቀረበችው አቤቱታ ምክንያታዊነት የጎደለው ነው ብለዋል።

የግብጽ አቤቱታ ኢትዮጵያ "የቅኝ ግዛት ውል" ተገዳ እንድትፈርም በማድረግ የአባይን ወንዝ በበላይነት ለመጠቀም ያላትን ፍላጎት እንደሚያሳይ ገልጸዋል።

እንደ ጥቁር አሜሪካዊው የመብቶች ተሟጋች ገለጻ "የናይል ወንዝ 85 በመቶ ከኢትዮጵያ፣ 15 በመቶ ከታችኛው ተፋፈስ አገራት የሚገኝ ሲሆን ግብጽ በወንዙ ላይ ምንም ድርሻ የላትም።" 

ግብጽ ለጸጥታው ምክር ቤት ያቀረበችው አቤቱታ ኢትዮጵያን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ውሃ ከመሙላት ለማስቆም እንደሆነ ተናግረዋል።

ይህ ግብጽ በናይል ወንዝ ያላትን የበላይነት አስተሳሰብ የሚያሳይ እንደሆነ ነው ጄሲ ጃክሰን ያስታወቁት።

ግብጽ ግዙፉን አስዋንን ስትገነባ፣ የግድቡን ውሃ ስትሞላ የኢትዮጵያን ፈቃድ እንዳልጠየቀችና ኢትዮጵያም ይሁንታ እንዳልሰጠች አውስተዋል።

"ነገሩን የባሰ የሚያደርገው" ይላሉ ጄሲ ጃክሰን 85 በመቶ የናይል ወንዝ ድርሻ እያላት የወንዙን አቅጣጫ በመቀየር ከተፋሰሱ አገራት ውጪ ለሆነ ተግባር ስትጠቀም ኢትዮጵያን አላማከረችም ብለዋል።

ይህም ድርጊት ዓለም አቀፍ የድንበር ተሻጋሪ ወንዝ ህጎችን የጣሰ እንደሆነ አስገንዝበዋል።

ግብጽ እ.አ.አ 1929 እና 1959 የተፈረሙ የቅኝ ግዛት ስምምነቶች ተጠብቀው እንዲቆዩላት ባላት ፍላጎት ከዚህ ቀደም አፍሪካዊ መሰረት ካላቸው የናይል ወንዝ ድርድሮች ራሷን ማግለሏ የሚታወቅ እውነት ነው ሲሉ ለኮሚቴው ሊቀመንበር ገልጸዋል።  

የግብጽ አቤቱታ በአሜሪካና በዓለም ባንክ አደራዳሪዎች አማካኝነት ኢትዮጵያ ግድቡን በመሙላት የተቀመጠውን ስምምነት አላከበረችም የሚል አንድምታ ያለው እንደሆነም አመልከተዋል።

ከዚህም አኳያ የአሜሪካ መንግስትና የዓለም ባንክ ኢትዮጵያና ግብጽ በተለያየ ዓለም አቀፍ ህግ ይዳኛሉ ብለው ካላሰቡ በቀር ግብጽ ያላደረገችውን ነገር ኢትዮጵያን አድርጊ መባል እንደሌለባት ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን አስመልክቶ እያደረገች ያለው ሁሉም ነገር ዓለም አቀፍ የውሃ ህጎችን የተከተለ ነውም ብለዋል ጄሲ ጃክሰን።

አሜሪካና የዓለም ባንክ  በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ታዛቢዎች እንደሆኑ መግለጻቸው ይታወቃል።

በዓለም አቀፍ የድርድር ህጎች ሁሉም ተደራዳሪ አካላት ካልፈቀዱ በስተቀር ታዛቢዎች ህጋዊ አስተያየትና ምክረ ሀሳብ ማቅረብ እንደማይችሉም ነው ጄሲ ጃክሰን ያስረዱት።

ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ ለአሜሪካና ለዓለም ባንክ የግድቡን ድርድር አስመልክቶ ህጋዊ አስተያየትና ምክረ ሀሳብ ያካተተ ህጋዊ አስተያየት እንዲያወጡ ፈቃድም ሆነ ይሁንታ እንዳልሰጠች አመልክተዋል።

በዚህ መሰረት የአሜሪካ መንግስትና የዓለም ባንክ ግድቡን አስመልክቶ ህጋዊ አስተያየቶችን አዘጋጅተው ከሆነ ይሄ ተግባር በታዛቢነት የነበራቸውን ግዴታ በከፍተኛ ሁኔታ መጣስ ነው ብለዋል።

የአሜሪካ መንግስትና የዓለም ባንክ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ሁለት ጉዳዮችን የማስረዳት ህጋዊና ሞራላዊ ግዴታ እንዳለባቸውም የ78 ዓመቱ የመብቶች ተሟጋች ጄሲ ጃክሰን ገልጸዋል።

የመጀመሪያው በህዳሴው ግድብ ድርድር ላይ የአሜሪካ ግምጃ ቤትና የዓለም ባንክ ታዛቢዎች ነን በሚል ራሳቸውን ያቀረቡበት ሁኔታ "ውሸት" መሆኑን ማሳወቅ እንዳለባቸውም ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ አስታራቂ በሆነ መልኩ ተሻሽሏል የተባለውን ስምምነት ለመፈረም ፈቃደኛ አልሆነችም የሚለው ሀሳብ ትክክል እንዳልሆነ መግለጽ ደግሞ ሁለተኛው ግዴታቸው እንደሆነ አመልክተዋል።

ይህ ሀሳብ ወደተሳሳተ መንገድ የሚመራና ኢትዮጵያ ለሁለቱ አካላት አስታራቂ ሀሳብ በሚል ስምምነቱ እንዲሻሻል የሰጠችው ይሁንታና ፈቃድ እንደሌለም አብራርተዋል።

አሜሪካ የዓረብ ሊግና ግብጽ "የቅኝ ግዛት ስምምነትን" በአፍሪካ አገራት ላይ ለመጫን ያላቸውን ውጥን በግልጽ መረዳት እንደሚገባት ጄሲ ጃክሰን አስረድተዋል።

ጥቁር የአሜሪካ ኮንግረስ አባላት ኮሚቴ በግብጽ ላይ ጠንካራ የውሳኔ ሀሳብ እንዲያወጣም ጄሲ ጃክሰን ጠይቀዋል።

ዋና መቀመጫውን ዋሽንግተን ዲሲ ያደረገው የጥቁር የአሜሪካ ኮንግረስ አባላት ኮሚቴ እ.አ.አ በ1971 የተቋቋመ ነው።

ኮሚቴው አሁን የአሜሪካ ኮንግረስና ሴኔት አባላት 55 የዴሞክራቲክ ፓርቲ ፖለቲከኞችን የያዘ ሲሆን ለጥቁር አሜሪካዊያንና ሌሎች የተገለሉ ማህበረሰቦች በአሜሪካ ፍትሃዊ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ ላይ ትኩረቱን አድርጎ ይሰራል።

መቀመጫውን በቺካጎ ግዛት ያደረገው የሲቪክ መብቶች ተቋም "ሬንቦው ፑሽ ኮሊሽን" እ.አ.አ በ1996 ጥቁር አሜሪካዊው የመብቶች ተሟጋች ጄሲ ጃክሰን "ሬንቦው" እና "ፑሽ" የሚባሉትን የራሳቸውን ተቋማት በማዋሃድ የመሰረቱት ነው።

ተቋሙ የጥቁርና የአፍሪካ አሜሪካዊያን መብት እንዲከበር የሚሰራ እንደሆነም መረጃዎች ያመለክታሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም