የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከል ላይ በማተኮር ለተዘጋጀው የፈጠራ ስራ ውድድር የዕውቅና ፕሮግራም እየተካሄደ ነው

94

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 13/2012 ዓ.ም ( ኢዜአ) የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝ መከላከል ላይ በማተኮር ለተዘጋጀው የፈጠራ ስራ ውድድር የዕውቅና ፕሮግራም ዛሬ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይን ጨምሮ የተጠሪ ተቋማት ኃላፊዎች፣ ተጋባዥ  እንግዶችና የፈጠራ ባለሙያዎች ተገኝተዋል።

ወረርሽኙን ለመግታትና ለመከላከል አዳዲስ ምርምሮችን ማካሄድና የወጣቶችን መነሳሳት በተደራጀ አግባብ ለመምራት ውድድሩ መዘጋጀቱ ተገልጿል።

በዲጂታልና አይሲቲ፣ በፈጠራና ኢኖቬሽንና በጂኦ ስፓሻል ሶስት ዘርፎች 12 የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ፕሮጀክቶችን ወደ ውጤት ለመለወጥ ዕውቅና ይሰጣል።

በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ለታወከው ዕለታዊ የስራ እንቅስቃሴ መፍትሔ የሚሆኑና የሚፈጠረውን ጫና የሚቀንሱ ለምሳሌ በትምህርት፣ በቢሮ ስራና በሌሎች እንቅስቃሴዎች በአጠቃላይ የስራ ባህል ለውጥ የሚያመጡ ፈጠራዎች መሆናቸው ተገልጿል።

ሚኒስቴሩ ወደ ፊትም የፈጠራ ስራዎችን እንደሚያበረታታም ተጠቁሟል።

ከ5 ተቋማት የተውጣጡ አባላት ያለው ኮሚቴ የቀረቡ የፈጠራ ስራዎችን እንደመዘነም ተነግሯል።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከሰቱን ተከትሎ በርካታ የፈጠራ ሰዎች ወረርሽኙን ለመከላከል የሚያግዙ የፈጠራ ስራዎችን ማቅረባቸው ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም