በባህላዊ መንገድ ማዕድናትን በማምረት ተጠቃሚ መሆናቸውን ወጣቶች ተናገሩ

53
ሽሬ እንዳስላሴ  ሚያዚያ 30/2010 በትግራይ ሰሜናዊ  ምዕራባዊ ዞን  በባህላዊ መንገድ ወርቅና ሌሎች ማዕድናትን እያመረቱ ከሽያጩ በሚያገኙት ገቢ ኑሮቸውን እያሻሸሉ መሆናቸውን በማህበር ተደራጅተው  ወደ ስራ የገቡ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ወጣቶች ተናገሩ፡፡ በዞኑ አስገደ ፅምብላ ወረዳ 26 ወጣቶች  ብሩህ ተስፋ በሚል ስያሜ በማህበር ተደራጅተው በባህላዊ መንገድ ወርቅ በማምረት ስራ  ከተሰማሩ መካከል ይገኙበታል፡፡ የማህበሩ አባል ወጣት መብራህቶም አረጋዊ እንደገለጸው በባህላዊ መንገድ ደለል ወርቅ  የማምረት ስራ አድካሚና አስቸጋሪ ቢሆንም ለውጥ እንዳገኙበት ተናግሯል፡፡ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ለብሔራዊ ባንክ ካቀረቡት 1ሺህ 390 ግራም ወርቅ  ሽያጭ የማህበሩ አባላት በነፍስ ወከፍ ከ40ሺህ ብር በላይ ገቢ ማግኘታቸውን አመልክቷል፡፡ በላእላይ አዲያቦ ወረዳ  24 ወጣቶችን በአባልነት አቅፎ  የሚንቀሳቀሰው የዓቅሊ የደለል ወርቅ አምራቾች ማህበር አባል ወጣት ህሉፍ በበኩሉ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከባህላዊ ወርቅ ምርት ሽያጭ በግሉ ከሦስት መቶ ሺህ  ብር በላይ ገቢ ማግኘቱን ገልጿል፡፡ ወጣቱ እንደገለጸው  በአዲ ዳዕሮ ከተማ ባለ አምስት ክፍል ቤት ገንብቶ በየወሩ ከአምስት ሺህ  ብር በላይ በማከራየት ተጨማሪ ገቢ እያገኘ ኑሮውን እያሻሻለ ነው፡፡ ሌላው የማህበሩ አባል ወጣት ሃይለስላሴ በላይ በሰጠው አስተያየት ከደለል ወርቅ ሽያጭ 280 ሺህ ብር በማግኘት ተጠቃሚ  መሆኑን  ገልጿል፡፡ ተደራጅተው ለግንባታ የሚሆን ጥርብ ድንጋይ እያመረቱ ለሽያጭ በማቅረብ ሥራ የተሰማረው  ወጣት ህሉፍ ባህታ እንዳለው  በየቀኑ  ሰባት ጭነት መኪና  ድንጋይ ለተጠቃሚዎች ያቀርባሉ። በዚህም በሚያገኘው ገቢ ኑሮውን በማሻሻል ተጠቃሚ መሆኑን ጠቅሷል፡፡ ለግንባታ የሚወል አሸዋ  በማምረት ላይ የተሰማራው ወጣት አሰፋ ተካ በበኩሉ በዚህ ስራ ከሚያገኘው ገቢ በየወሩ ሦስት ሺህ ብር  በመቆጠብ አሁን ላይ ከ72ሺህ ብር በላይ  ማድኘት እንደቻለ ተናግሯል። ወጣቶቹ  ቀደም ሲል ከነበረባቸው የስራ አጥነት ችግር ተላቀው በዘርፉ ልማት ተጠቃሚነታቸው እያደገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በዞኑ በባህላዊ ወርቅ ፣  ምርት፣በድንጋይ፣በጠጠርና በአሸዋ መምረት ስራ በ211 ማህበራት የተደራጁ 6ሺህ 810 ሰዎች   እንደሚገኙ በክልሉ ማዕድን ልማት ሀብት ኤጀንሲ  የማዕድን ዘርፍ አስተባባሪ አቶ ካልአዩ ብርሃነ ገልጸዋል፡፡ ከመካከላቸውም 2ሺህ 607 ሴቶች እንደሆኑ አመልክተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም