ጉባዔው ለዘላቂ ሠላምና ዋስትና ላለው ዴሞክራሲ አጋዥ የውሳኔ ሐሳቦችን ለማመንጨት ቁርጠኛ ነው

73

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 13/2012 ዓ.ም ( ኢዜአ) የሕገ-መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ለዘላቂ ሠላምና ዋስትና ላለው ዴሞክራሲ አጋዥ የውሳኔ ሀሳቦችን ለማመንጨት ቁርጠኛ መሆኑን ገለፀ።

ጉባዔው የሕገ-መንግስትን ትርጉም በተመለከተ ሲያካሂድ የቆየው የባለሙያዎች ሐሳብ መስጫ መርሃ ግብር ዛሬ ተጠናቋል።

ዘንድሮ ሊካሄድ ቀን ተቆርጦለት የነበረውን 6ኛው ብሔራዊ ምርጫ በኮቪድ-19 ሳቢያ ማካሄድ ስለማይቻል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እንዲራዘም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማቅረቡ ይታወቃል።

ምክር ቤቱም ከሕግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የቀረበለትን የመፍትሄ ሐሳብ በማፅደቅ ለሕገ-መንግስት አጣሪ ጉባዔ መላኩ ይታወሳል።

በመሆኑም የሕገ-መንግስት ትርጓሜ ለመስጠት ጉዳዩ የሚመለከታቸው የሕግና ምርምር ተቋማት፣ የሕገ- መንግስት ባለሙያዎች፣ ሕገ-መንግስት በማርቀቅ አስተዋጽኦ የነበራቸውና የሕግ ባለሙያዎችን ጨምሮ ውይይት ሲካሄድ ቆይቷል።

የሕገ-መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ የሕገ-መንግስትን ትርጉም በተመለከተ ሲያካሂድ የቆየው የባለሙያዎች ሐሳብ መስጫም ዛሬ ተጠናቋል።

በውይይቱ ማጠቃለያ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትና የሕገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ሰብሳቢዋ ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ ውይይቱ ሕገ-መንግሥታዊ ጥያቄዎች የጠራ ትርጉም እንዲያገኙ መልካም አጋጣሚ መፍጠሩን ተናግረዋል።

ምክር ቤቱ በኮቪድ-19 ምክንያት ምርጫ ቦርድ ምርጫው እንዲራዘም ያነሳውን ግዙፍ ሕገ-መንግስታዊ ጥያቄም ለሕገ-መንግስት አጣሪ ጉባዔ መላኩን ገልጸዋል።

ሕገ-መንግስቱ ምላሽ ያልሰጣቸውንና ትርጉም እንዲሰጥባቸው የተጠየቁትን የሕገ-መንግስቱን አንቀጾች  የሕግና ምርምር ተቋማት፣ የሕገ-መንግስት ባለሙያዎች፣ ሕገ-መንግስት በማርቀቅ አስተዋጽኦ የነበራቸውና የሕግ-ባለሙያዎችን በመጋበዝ ሰፊ ውይይት ማድረጉን አብራርተዋል።

ጉባዔው ባለሙያዎችን የጋበዘበትና በቴሌቪዥን በቀጥታ የተላለፈው መድረክ ከተጠበቀው በላይ ውጤታማ እንደነበርም አንስተዋል።

34 የጽሑፍ አስተያየት አቅራቢ ግለሰቦችና ተቋማት እንደነበሩና በአጠቃላይ በቡድን የተዘጋጁትን ጨምሮ 22 የጽሑፍ አስተያየቶች መቅረባቸውን ጠቅሰዋል።

የጉባዔው ባለሙያዎች የቀረቡትን ጽሑፎች ዋና ዋና ነጥቦችና ትንተናዎች በመለየት ላይ መሆናቸውን ጠቅሰው አብዛኛዎቹ አስተያየቶች ወደ ተመሳሳይ ድምዳሜ የሚያደርሱ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በአጭር ጊዜ ሂደቶችን አሳታፊ ለማድረግ መሞከሩን የገለጹት ወይዘሮ መዓዛ እንዲህ ያለው አዲስ ሂደትና የተቋም ግንባታ ጅምር እንቅስቃሴ ግድፈት አይኖረውም ለማለት እንደማያስደፍርም አክለዋል።

ይሁን እንጂ ትልቁ ነጥብ ግብዓቶችን ወስዶ ከፍ ያለና አብነት የሚሆን ስራ ለመስራት ከፍተኛ ፍላጎት መኖሩን አሳይቷል ነው ያሉት።

የሚሰጠው የውሳኔ ሐሳብ በሕግ ትንተና ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ሕገ-መንግስቱና የተቋቋመበት አዋጅ የሚደነግግ በመሆኑ ይህንን ተከትሎ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

በጉባዔው ሲካሄድ የቆየው ውይይት በመንግስት አስተዳደር የሕዝብን ተሳትፎ የማሳደግ ኃላፊነትን ተጨባጭ ስለሚያደርገው በዓርአያነት ሊወሰድ እንደሚገባም ገልጸዋል።

የሕገ-መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ አሁን ያየውንም ሆነ ወደፊት ለሚከሰቱ ጉዳዮች በአገሪቷ ዘላቂ ሠላምና ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ እንዲሰፍን አጋዥ ሀሳቦችን ለማመንጨት ቁርጠኛ ነው ብለዋል።

ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ዕድገት እንዲፋጠን፣ በሕግ የበላይነትና በፍትህ ላይ የተመሰረተ አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ለመፍጠር የሚያግዙ እሳቤዎችና የውሳኔ ሐሳቦችን ለማመንጨት ያለውን ቁርጠኝነትም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም