ለግብርና ቴክኖሎጂ ውጤቶች ተደራሽነት የተመራማሪዎችና ባለሙያዎች እገዛ ያስፈልጋል

159

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 11/2012(ኢዜአ) የግብርና ቴክኖሎጂ ውጤቶችን ተደራሽ ለማድረግ በዘርፉ ምርምር ያደረጉ ምሁራንና ባለሙያዎችን እገዛና ሃላፊነት እንደሚጠይቅ ተገለጸ፡፡ 

የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በሚያከናውናቸው የግብርና ምርታማነት ማሳደጊያ ምርምሮች አበረታች ውጤቶች እያስመዘገበ መሆኑን አስታውቋል።

ኢንስቲትዮቱ ይህን ያስታወቀው በዘርፉ ጥናትና ምርምር ካደረጉ ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት ጋር ዛሬ ባካሄደው ውይይት ነው።

በውይይቱ የባዮ-ቴክኖሎጂ ሳይንስ በዓለም ላይ እያስመዘገበ ያለውን ፈጣን ለውጥ ለኢትዮጵያ በሚመጥን መልኩ በመጠቀም ግብርናውን ማዘመንና ፈጣን እድገት ማምጣት በሚያስችሉ ጉዳዮች ምክክር ተደርጓል።

የግብርና ሚኒስትር አቶ ዑመር ሁሴንም ለኢትዮጵያ የሚመጥኑ ብሎም ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ የሚያስችሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ማሸጋገር ለነገ የማይባል ትልቅ የቤት ስራመሆኑን ተናግረዋል።

የግብርና ቴክኖሎጂ ውጤቶችን ተደራሽ ለማድረግም በዘርፉ ሰፊ ምርምር ያደረጉ ምሁራንና ባለሙያዎችን ሃላፊነት እንደሚጠይቅ አስገንዝበዋል።

የከተማ ግብርና ብዙም ያልተሰራበት ዘርፍ መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትሩ፤ በአዲስ አበባ በቴክኖሎጂ የታገዙ ግብዓቶችን በመጠቀም ምርታማነትን የሚያሳድጉ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም ገልጸዋል።

እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሳቢያ 8 በመቶ፣ በበረሃ አንበጣ ደግሞ 5 በመቶ የምርት መጠን መቀነስ ሊያጋጥም ይችላል።

በዚህ ምክንያትም 15 ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ ለችግር ሊጋለጥ ስለሚችል ጉዳቱን መከላከል የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት ስራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ማንደፍሮ ንጉሴ በበኩላቸው መስሪያ ቤታቸው በሰብል፣ በእንስሳት፣ በደቂቅ ነፍሳትና አካላት ላይ ስለሚያካሂዳቸው ምርምሮች አብራርተዋል።

ምርምሮቹ የሚካሄዱት በአገር አቀፍ ደረጃ በእንስሳትና በሰብሎች ላይ የሚያጋጥሙ ፈታኝ በሽታዎችን፣ ተባዮችና ነፍሳትን በመቀነስ ምርታማነትን ለማሳደግ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

በጥጥ፣ በበቆሎና በእንሰት ሰብሎች ላይ በተደረገ የዘረ-መል ምርምር ምርታማነታቸውን ማሳደግና የሚያጋጥማቸውን በሽታ መቋቋም የሚያስችል የምርምር ውጤት መገኘቱንም ገልጸዋል።

በጥጥ ላይ የሚከሰተውን 'አፍሪካን ቦል ዋርም' የተሰኘ በሽታ ማስወገድ የሚያስችል የዘረ-መል ምርምር በማካሄድ ምርቱን ማሳደግና በሽታውን መቋቋም የሚያስችል ውጤት ተገኝቷልም ብለዋል።

ለበቆሎ ቅርብ ከሆነ አዝርዕት ላይ የዘረ-መል ምርምር በማድረግ ምርቱን ማሳደግና የሚከሰተውን የግንደ ቆርቁር ትል መቋቋም የሚያስችል ውጤት መገኘቱንም ጠቅሰዋል።

በእንሰት ላይም እንዲሁ ከሙዝ ተክል በተወሰደ የዘረ-መል ምርምር ቅጠልና ግንዱን በማጠውለግ ምርቱ እንዲቀንስ የሚያደርገውን በሽታ መከላከል የሚያስችል ውጤት መገኘቱ ተረጋግጧል።

የኢንስቲትዩቱ የግብርና ባዮ-ቴክኖሎጂ ዳይሬክተር ዶክተር ታደሰ ዳባ እንደገለጹትም የዘረ-መል ምርምር የተደረገባቸው እንደ ጥጥ፣ በቆሎና እንሰት ያሉ ሰብሎችን ምርታማነት የሚያሳድግ፣ ድርቅና በሽታን መቋቋም የሚያስችል ውጤት ተገኝቷል።

በግብርና ሚኒስትሩ በተመራው ውይይት በዘርፉ የተለያዩ ምርምሮችን ያደረጉ ባለሙያዎች በአካልና በቪዲዮ በመታገዝ ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም