በኦሮሚያ ክልል ለሚገኙ መምህራን የሙያ ብቃት ምዘና ሊሰጥ ነው

75
አዳማ ሰኔ 28/2010 በኦሮሚያ ክልል ለሚገኙ መምህራን የሙያ ብቃት ምዘና ለመስጠት ዝግጅት ማጠናቀቁን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ። የቢሮ ኃላፊው ዶክተር ቶላ በሪሶ ለኢዜአ እንደገለጹት በክልሉ የትምህርት ዘርፍ ለሚታየው የጥራት ችግር የመምህራን የብቃት ማነስ ተጠቃሽ ነው። በክልሉ ከ185 ሺህ በላይ የሚሆኑ መምህራን እንደሚገኙ አመልክተው “ሁሉም መምህራን ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በሙያ ብቃት ምዘና ውስጥ እንዲያልፉ ይደረጋል'' ብለዋል። ምዘናውን የማልፉ መምህራን ስልጠናና የክህሎት አቅም ግንባታ ወስደው በድጋሜ እንደሚመዘኑ ገልፀዋል፡፡ የክልሉ መምህራንም ይህን ተገንዘበው ራሳቸውን በበቂ ሁኔታ ማዘጋጀት እንደሚገባቸው አመልክተዋል። በክልሉ ትምህርት ቢሮ የእቅድ ዝግጅት ግምገማና ግብረ መልስ ቡድን መሪ አቶ ደሳለኝ ዋቅጅራ በበኩላቸው በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት የሙያ ብቃት ምዘና ከወሰዱት 17ሺህ በላይ መምህራን ውስጥ 18 በመቶ ብቻ ምዘናውን ማለፋቸውን ገልጠዋል። “የመምህራን የብቃት ማነስ ብቁና ተወዳዳሪ የሰው ሃይል ለማፍራት የሚደረገውን ጥረት አደጋ ላይ የሚጥል ከመሆኑም ባሻገር በአሁኑ ወቅት ጥያቄ ውስጥ የገባው የትምህርት ጥራት ችግር መፍትሄ እንዳያገኝ ያደርጋል'' ብለዋል። የትምህርት ጥራት ለማስጠበቅ መምህራን በሙያ ምዘና ውስጥ ማለፍ ወሳኝ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በአርሲ ዞን ጎሎልቻ ወረዳ የሰበታ ትምህርት ቤት መምህር ቱራ ቃስም ናቸው። “ለትምህርት ጥራት ችግር ዋናውን ድርሻ መያዝ ያለበት አስተማሪው ነው'' ያሉት መምህሩ ከመማሪያ ግብዓት በተጨማሪ በሚያስተምረው ትምህርት በቂ እውቀትና ክህሎት ሊኖረው እንደሚገባ ጠቁመዋል። ሌላኛው አስተያየት ሰጪ በአርሲ ዞን ጮሌ ወረዳ ሞዬ ጋዶ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ ሙስጠፋ ሀሰን በበኩላቸው የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ በትምህርት ቤቱ የጥራት ክበባት ከማደራጀት ጀምሮ ተስፋ ሰጪ ተግባራት እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል። “የመምህራን የሙያ ብቃትን ለማረጋገጥ አስገዳጅ የምዘና ሥርዓት መዘርጋቱም የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ  ፋይዳው የጎላ ነው'' ብለዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም