በበሬሳ ወንዝ ላይ በ21 ሚሊዮን ብር የተገነባው ድልድይ ለአገልግሎት ክፍት ሆነ

83
ደብረ ብርሃን ሰኔ 28/2010 በደብረ ብርሃን ከተማ የሚገኘው በሬሳ ወንዝ ላይ በ21 ሚሊዮን ብር የተገነባው ድልድይ ለአገልግሎት ክፍት ሆነ። ዛሬ በተካሄደው የድልድዩ ርክክብ ስነስርአት ላይ እንደተገለጸው ድልድዩ 32 ሜትር ርዝመትና 24 ሜትር ስፋት አለው ። የደብረ ብርሃን ከተማ ቤቶች፣ ልማትና ኮንስትራክሽን አገልግሎት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሰለሞን ጌታቸው በርክክቡ ላይ እንዳሉት የበሬሳ ወንዝ መሻገሪያ ድልድይ ለከተማዋ አመራጭ መተላለፊያ ሆኖ ያገለግላል። ከዓለም ባንክ በተገኘ 21 ሚሊዮን ብር ወጪ ድልድዩ መገንባቱን ጠቁመው፣ ግንባታው በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በውሉ መሰረት መጠናቀቁን ተናግረዋል። በልድዩም በቀን ከ15 ሺህ እስከ 20 ሺህ ሰው እንደሚተላፍበት ተናግረዋል። ቀደም ሲል ድልድይ ይሰራልን በሚል ከህዝቡ በተደጋጋሚ ለተነሳው ጥያቄ ምላሽ ባለመሰጠቱ የመልካም አስተዳደር ችግር ሆኖ መቆየቱንም አቶ ሰለሞን አስታውሰዋል። የድልድዩ መገንባት ከአዲስ አበባ ወደ ደሴና መቀሌ ለሚሄዱ ተሽከርካሪዎች አማራጭ መተላለፊያ እንዲሆን ከሞረትና ጅሩ መገንጠያ እስከ ደሴ መውጫ አኳሴፍ ውሃ ፋብሪካ ድረስ 6 ኪሎ ሜትር የጠጠር መንገድ መሰራቱን ተናግረዋል። የድልድዩን ግንባታ ያከናወነው "ኪዳነ አክሊል ጠቅላላ ሥራ ተቋራጭ" ሥራ አስኬያጅ አቶ ታምራት ታደሰ በበኩላቸው ግንባታውን በታቀደለት የጊዜ ገደብ ውስጥ ሰርተው ማጠናቀቃቸውን ገልጸዋል፡፡ በግንባታ ሥራው የሕብረተሰቡ ተሳትፎ ከፍተኛ መሆኑ በጊዜው ለማጠናቀቅ ጉልህ ድርሻ ማበርከቱም ጠቁመው ድልድዩ ለቀጣይ 40 ዓመታት ማገልገል እንደሚችል አመልክተዋል። በደብረ ብርሃን ከተማ የቀበሌ 07 ነዋሪ መምህር ለማ አየለ ከዚህ ቀደም በወንዙ ላይ ድልድይ ባለመሰራቱ በሌላ አካባቢ ሄዶ ለመሻገር የአንድ ሰዓት የእግር ጉዞ መጓዝ ግድ ይላቸው እንደነበር አስታውሰዋል። በእንጨት ጊዜያዊ  የመሸጋገሪያ ድልድይ በተደጋጋሚ ቢሰራም በክረምት ጎርፍ እየወሰደው ሲቸገሩ መቆየታቸውን ገልጸው፤ በድልድዩ የረጅም ጊዜ ጥያቄያቸው በመፈታቱ እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም