በጌዴኦ ዞን የአትሌቲክስ ስፖርትን ለማሳደግ ድጋፍ ተደረገ

65

ዲላ፣ ግንቦት 11/2012 (ኢዜአ) የጌዴኦ ዞን ባህል ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ በዞኑ ለሚገኙ የአትሌቲክስ ፕሮጀክቶች ማጠናከሪያ 200 ሺህ ብር የሚገመት የስፖርት ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።

በዞኑ በአትሌቲክስ ዘርፍ ውጤታማ ስፖርተኞችን ለማፍራት አቅምና ምቹ የአየር ንብረት ያላቸው ወረዳዎች ተለይተው ወጣቶችን የማብቃት ስራ እየተከናወነ መሆኑንም መምሪያው አስታውቋል።

የጌዴኦ ዞን ባህል ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ የስፖርት ዘርፍ ሃላፊ አቶ የምስራች ዳካ ለኢዜአ እንዳሉት መምሪያው በስፖርት ዘርፍ የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥና ተተኪ ስፖርተኞችን በማፍራት ረገድ በትኩረት እየሰራ ነው።

በዞኑ እግር ኳስን ጨምሮ በቮሊቦል ፣ በቅርጫት ኳስና በካራቴ የስፖርት ዘርፎች 19 የታዳጊ ፕሮጀክቶችን በማቋቋም ከ2 ሺህ በላይ ታዳጊ ወጣቶች በመሰልጠን ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

በተለይ በአትሌቲክሱ ዘርፍ ውጤታማ አትሌቶችን ለማፍራት በዞኑ አቅምና ምቹ የአየር ንብረት ያላቸው የቡሌና ገደብ ወረዳዎች ተለይተው ወጣቱን የማብቃት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።

በተጠቀሱ ወረዳዎች ለታቀፉ 50 አትሌቶችና አሰልጣኞች የስፖርት ቁሳቁስና የገንዘብ ድጋፍ መደረጉንም ገልጸዋል።

ድጋፉ ለአትሌቶቹ የመለማመጃና የመወዳደሪያ ጫማና ሙሉ ትጥቅን እንዲሁም ለአሰልጣኝ ቡድን አባላት ሙሉ ትጥቅና የላብ መተኪያ ገንዘብን ያካተተ ሲሆን በአጠቃላይ 200 ሺህ ብር ወጭ መደረጉንም ተናግረዋል።

የኮሮና ቫይረስ መከሰት የስፖርት እንቅስቃሴን ማቀዛቀዙን የተናገሩት አቶ የምስራች አትሌቶች በግል የሚያደርጉትን ልምምድ መቀጠል እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ድጋፉን ካገኙት መካከል ወጣት አዛለች አለማየው እንዳለችው በዞኑ ቡሌ ወረዳ እሷን ጨምሮ 25 ወጣቶች ካለፈው አመት ጀምሮ በአትሌትክስ ዘርፍ በፕሮጀክት ታቅፈው ልምምድ እያደረጉ መሆናቸውን ገልጻለች።

ይሁንና የኮሮና ቫይረስ መከሰቱን ተከትሎ የጋራ ልምምድ ከመቆሙም ባለፈ በግል ልምምድ ለማድረግ የትጥቅ ችግር እንቅፋት ሆኖባት መቆየቱን ተናግራለች።

ይህን በማየት የዞኑ ባህል ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ያደረገው ድጋፍ ችግሩን እንደፈታላቸው ጠቁማ በግል የምታደርገውን ልምምድ አጠናክራ እንደምትቀጥል አስታውቃለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም