"ኢትዮጵያ የምትከተለው ፓርላሜንታዊ ሥርዓት፤ መንግሥት የሥልጣን ዘመኑ ስላበቃ ብቻ እንዲወርድ የሚፈቅድ አይደለም"...ምሁራን

187

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 8/2012 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ የምትከተለው ፓርላሜንታዊ ሥርዓት፤ መንግሥት የሥልጣን ዘመኑ ስላበቃ ብቻ ከሥልጣኑ እንዲወርድ የሚፈቅድ አይደለም ሲሉ ምሁራን ገለጹ።

የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ የሕገ መንግሥት ትርጉምን በተመለከተ ያዘጋጀው የባለሙያዎች ሀሳብ መስጫ መድረክ በዛሬው ዕለት ተካሂዷል።

የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቀረበለት የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄ  ምላሽ ለመስጠት የባለሙያዎችን ሀሳብ እየተቀበለ ይገኛል።

የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 54 እና 58 ሥልጣን ላይ ያለ መንግሥት የሥልጣን ዘመን የሚያበቃው በአምስት ዓመት መሆኑን ያስቀምጣል።

በአንቀጽ 93 ደግሞ ከአቅም በላይ የሆነ አደጋ፤ የውጭ ወረራ፣ ሕገ መንግሥቱን አደጋ ላይ የሚጥል ችግርና በሽታ ሲከሰት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጅ እንዳለበት ተቀምጧል።

በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ  ምክንያት የሕዝብ ጤንነት አደጋ ላይ የሚጥል በሽታ በመሆኑ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጇል።

የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን አርዳ በኩል የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 54 እና 58 የተቀመጠውና አንቀጽ 93 ተቃርኖ አላቸው፤ እንዴትስ ይታረቃሉ? የሚል ጥያቄ አንስተዋል።

የሕግ ምሁሩ ፕሮፌሰር ዮናታን ተስፋዬ በሰጡት ምላሽና አስተያየት የኢትዮጵያ መንግሥት ፓርላሜንታዊ ነው።

ፓርላሜንታዊ መንግሥት ደግሞ ሥልጣን ላይ ያለ መንግሥት የሥልጣን ዘመኑ ስላበቃ ብቻ ከሥልጣን አይወርድም ይላሉ።

ይልቁንስ ሥልጣኑን የሚረከብ መንግሥት ሲኖር ብቻ ከሥልጣን እንደሚለቅ ነው ያብራሩት።

በመሆኑም አሁን ያለው መንግሥት የሥልጣኑ ዘመን ስላበቃ ብቻ ከሥልጣን ወርዶ ሀገሪቱ ያለመንግሥት እንድትቆይ የሚጋብዝ አለመሆኑን አስረድተዋል።

የፌዴራሊዝምና መልካም አስተዳደር ምሁሩ ዶክተር ዘመላክ አይተነው እንዳሉትም ሕገ መንግሥቱ በቀጥታ ከጠቅላላ ዓላማ አንጻር ሊተረጎም ይችላል።

በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥቱ ሲተረጎም ሕዝብን በሚጠቅምና ስሜት በሚሰጥ እንዲሁም ምክንያታዊ በሆነ መልኩ ሊሆን ይገባልም ብለዋል።

ይህ ሲባል ግን ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት እንደፈለገው ለረጅም ዓመት ሥልጣን ላይ ለመቆየት በሚፈቅድ መልኩ ሳይሆን ነበራዊ ሁኔታን ግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ ሊሆን ይገባል ብለዋል።

በዛሬው ዕለትም በሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ አዘጋጅነት የሕግና ምርምር ተቋማት፣ የሕገ መንግሥት ባለሙያዎች፣ ሕገ መንግሥት በማርቀቅ አስተዋጽኦ የነበራቸው ባለሙያዎችና የሕግ ባለሙያዎች የተሳተፉበት የውይይት መድረክ ተካሂዷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም