ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት የማሽላ ምርምር ውጤት ወደ ተግባር አልገባም

340

አዲስ አበባ ግንቦት 7/2012 (ኢዜአ) መንግስት ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ያደረገበት የማሽላ ምርምር ውጤት በሁለት አካላት አለመግባባት ወደ ተግባር ሊለወጥ ሳይችል መቅረቱ ተገለፀ።

ከሁለት ዓመት በፊት የተገኘው የማሽላ ምርምር ውጤት ተመራማሪዎቹንና የግብርና ምርምር ኢንስትቲዩትን እያወዛገበ ይገኛል።

የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ መገናኛ ብዙሃንን ቀልብ የገዛውና ከ35 አመታት የላቀ የምርምር ትግልን የጠየቀው የማሽላ የምርምር ውጤት እስካሁን ተግባራዊ አለመደረጉ አነጋጋሪ ሆኗል። 

ተመራማሪ ሎሬት ታለጌታ ልዑል እንዳሉት፤ አንድ ጊዜ ተዘርቶ በአመት ከሁለት እስከ ሶስት ጊዜ ምርት የሚሰጠውና ድጋሚ ማረስና መዝራት ሳያስፈልግ ለሰባትና ከዚያ በላይ ዓመታት ምርት ሊሰጥ የሚችለው የማሽላ የምርምር ውጤት ሌሎች ጠቀሜታዎችን ይዟል።

በሄክታር ከ60 እስከ 75 ኩንታል ምርት እንደሚሰጥ የታመነበት የምርምር ውጤቱ ይፋ ከተደረገ ሁለት ዓመት ቢሆነውም በተመራማሪዎቹና በግብርና ምርምር ኢንስትቲዩት አለመግባባት ምክንያት እስካሁን ድረስ ወደ ተግባር አልተቀየረም።

ይህ ሊሆን የቻለው ከምርምር ተቋም ጋር መስማማት ባለመቻሉ እንደሆነ ሎሬት ታለጌታ ገልጸዋል።

”ከተመራማሪዎቹ ጋር ተደጋጋሚ ውይይት አድርጌያለሁ” የሚሉት በግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የብሔራዊ ማሽላ ምርምር ፕሮግራም አስተባባሪ ዶክተር ታዬ ታደሰ፤ ስራውን በሙከራ ለማረጋገጥ ሁለት አማራጮችን አቅርቦ ፈቃደኝነት እንዳጣ ገልፀዋል።

ተመራማሪው ሎሬት ታለጌታ አብሮ ለመስራት ያለው ህግ እንቅፋት መሆኑንም አረጋግጠዋል።

በሃገራችን በተለያዩ የአየር ንብረት ባላቸው አካባቢዎች ቢዘራ ምርት ሊሰጥ የሚችለው የምርምር ውጤቱ የመንግስት ሁለት ሚሊዮን ብር መዋዕለ ንዋይን ጠይቋል።

ሌላኛው ረዳት ተመራማሪ አቶ አብራሃም ቱራ ምርቱን ለመጠቀም የባዕድ ሃገራት ጥያቄ ተደጋግሞ እየተሰማ ነውና የመንግስት ቁርጠኛ ውሳኔ ግድ የሚልበት ጊዜ ላይ ተደርሷል። 

ዶክተር ታዬ በበኩላቸው እንደተቋም ቴክኖሎጂ ይዞ ለሚመጣ አካል ድጋፍ እንደሚደረግ ገልጸዋል።

የምርምር ተቋሙ ግን ባላረጋገጥኩት ነገር ላይ ሃሳብ መስጠት አልችልም ውሳኔዉ የባለ መብቱ ነው ይላል።