ከኢትዮ-ቴሌኮም ተገቢውን አገልግሎት እያገኘን አይደለም … የጅግጅጋ ከተማና አከባቢው ደንበኞች

58
ጅግጅጋ ሚያዚያ 30/2010 በኢትዮ-ቴሌኮም የአገልግሎት ጥራት መጓደል ቅሬታ እንደፈጠረባቸው አስተያየታቸውን የሰጡ የጅግጅጋ ከተማና አካባቢዋ ደንበኞች ገለጹ፡፡ የኢትዮ - ቴሌኮም ከፍተኛ አመራሮች በአገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ ከጅግጅጋ ከተማ ደንበኞች ጋር  ውይይት አካሂደዋል፡፡ በኔት ዎርክ ጥራት መጓደል ምክንያት በሞባይል ተጠቃሚዎች፣ በኢንተርኔት ካፊ፣ በፋይናንስ ተቋማት፣ በገቢ ሰብሳቢ መስሪያ ቤቶችና በትምህርት ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ እንቅፋት እየፈጠረ መሆኑን በውይይቱ የተሳተፉ ደንደበኞች ገልፀዋል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጅግጅጋ ቅርንጫፍ ተወካይ አቶ ዘላለም አዲሱ እንዳሉት በኔትወርክ መቆራረጥ ምክንያት ባንኩ ለደንበኞች ተገቢውን አገልግሎት እንዳይሰጥ እንቅፋት እየፈጠርባቸው ነው፡፡ ባንኩ አዳዲስ አገልግሎቶችን ለማስተዋወቅና የደንበኞችን እርካታ ለማሳደግ በሚያደርገው ጥረትም ተጽእኖ እያሳደረ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ "አንድ ብልሽት ካስመዘገብን በኋላ 24 ሰዓት ጠብቁ እንባላልን፣ ለፋይናንስ ተቋም 24 ሰዓት ከፍተኛ ኪሳራ ነው" ያሉት አቶ ዘላለም በሚቀርበው የአገልግሎት  ጥራት መጓደል ምክንያት ተወዳዳሪ መሆን አለመቻላቸውን ተናግረዋል፡፡ የከተማው ነዋሪ አቶ አብዲራህማን ኢልያስ በሰጡት አስተያየት በሚኖሩበት አካባቢ የሞባይል ኔትዎርክ የመቆራረጥና አንዳንድ ጊዜም ረዘም ላለ ጊዜ ጠፍቶ የመቆየት ሁኔታ እንደሚያጋጥማቸው አስታውቀዋል፡፡ ድርጅቱ የኔትወርክ ዝርጋታ ሲያከናወንም የከተማዋን ውበት በሚያበላሸ መልኩ ገመዶችና ሌሎች የድርጅቱ ንብረቶች በየቦታው የመዝረከረከ ሁኔታ ማስተዋላቸውን ገልፀዋል፡፡ የኢንተርኔት ካፊ ባለቤት ወጣት ፋራህ አደን በበኩሉ በየጊዜው የሚከሰተው የኔትወርክ ጥራት ችግር በስራው ላይ እንቅፋት እንደሆነበት ገልጿል፡፡ ከኢትዮ - ቴሌኮም የኮርፖሬት ኔትዎርክ ተወካይ አቶ አስጨናቂ ወሰን በውይይቱ ላይ በሰጡት ምላሽ ደንበኞች ያነሱትን የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር ለመፍታት ድርጅቱ  እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ለሞባይል ኔትወርክ መቆራረጥ እና አለመስራት ዋና ምክንያት የኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጥና በተለያየ ምክንያት የፋይበር መቆረጥ፣  የመለዋወጫ እጥረት ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል። ይህንን ችግር ለመፍታት የማስፋፊያ ፕሮጀክት ለማከናወን መታቀዱን ነው ተወካዩ የገለፁት፡፡ የኢትዮ - ቴሌኮም ጅግጅጋ ሪጅን ኃላፊ አቶ መሐመድ ሰኢድ በበኩላቸው የኢንተርኔት አገልግሎት ችግር በሚያጋጥምበት ወቅት የጥገና አገልግሎቱ የሚሰጠው ባለሙያዎችን ከድሬዳዋ በማስመጣት እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ በዚህም ለደንበኞች ፈጣን ምላሽ ባለመሰጠቱ ቅሬታ እየተፈጠረ መሆኑን አስታውቀዋል ችግሩን ለማስወገድ በቀጣይ  በ100 ኪሎ ሜትር ርቅት ውስጥ ለሚገኙ ደንበኞች የጥገና አገልግሎት የሚሰጥ  የባለሙያዎች ቡድን እንደሚደራጅ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም