በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የሳተላይት ማምረቻ መገጣጠሚያ ማቀናጃና መፈተሻ ፋብሪካ ግንባታ በሚቀጥለው ዓመት ይጀመራል

85

 አዲስ አበባ  ግንቦት 5/2012 (ኢዜአ) 50 ሚሊዮን ዩሮ ወጪ የሚደረግበት በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የሳተላይት ማምረቻ መገጣጠሚያ ማቀናጃና መፈተሻ ማዕከል ግንባታ በሚቀጥለው ዓመት ይጀመራል።

ግንባታው በ30 ወር ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሏል።

የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይስንስ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት እና የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ማዕከል ለመገንባትና በተለያዩ መስኮች ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል።

የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሰለሞን በላይ እና የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ደረጀ እንግዳ ስምምነቱን ተፈራርመዋል።

የሳተላይት ማምረቻ መገጣጠሚያ ማቀናጃና መፈተሻ ማዕከሉ የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ቅጥር ግቢ ውስጥ የሚገነባ ሲሆን 50 ሚሊዮን ዩሮ ወጪ ይደረግበታል።

የኢትዮጵያ መንግስት 10 ሚሊዮን ዩሮ ወጪውን የሚሸፍን ሲሆን የፈረንሳይ መንግስት 15 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍና ብድር እንዲሁም በአውሮፓ ህብረት ስር የሚገኘው የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ 25 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍና ብድር አድርገው የግንባታውን ወጪ ይሸፍናሉ ተብሏል።

ግንባታውን የፈረንሳዩ የኤሮስፔስ፣ የቢዝነስ፣ የመከላከያ የደህንነት መሳሪያዎች አምራች አሪያንግሩፕ ያከናውናል።

ማዕከሉ ሲጠናቀቅ ከትንሽ መጠን ጀምሮ እስከ 500 ኪሎ ግራም የሚመዝኑ 15 ሳተላይቶችን ያመርታል ተብሏል።

የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሰለሞን በላይ ኢትዮጵያ ወደ ህዋ ሳይንስ ዘርፍ ለመግባት ፖሊሲና የዘርፉ መሰረተ ልማቶች እንደሚያስፈልጓት ገልጸዋል።

''የማዕከሉ መገንባት የህዋ ኢንዱስትሪን ለማሳደግና የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲፈጠር አስተዋጽኦ ያደርጋል'' ብለዋል።

በማዕከሉ የሚመረቱ መሳሪያዎች ለህዋ ብቻ ሳይሆን ለሌሎች የኢንዱስትሪ ስራዎች እንደሚውሉ ተናግረዋል።

በቀጣይም ከአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በተጨማሪ በክልሎች ማዕከሎች እንደሚገነቡም አመልክተዋል።

የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ደረጀ እንግዳ በበኩላቸው ''በስምምነቱ መሰረት ሁለቱ ተቋማት በህዋ ዘርፍ ጥናትና ምርምር ያደርጋሉ'' ብለዋል።

ዩኒቨርሲቲው በዘርፉ የድህረ ምረቃ ትምህርት እንደሚሰጥ ገልጸዋል።

በሚቀጥለው ዓመት አጋማሽ በተወሰኑ ተማሪዎች ትምህርቱን ለመጀመር እቅድ እንዳለና የኢንስቲየዩቱ፣ የዩኒቨርሲቲውና የዘርፉ ባለሙያዎች ትምህርቱን እንደሚሰጡ ተናግረዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይ ''የማዕከሉ ግንባታ ኢትዮጵያ በራሷ አቅም ሳተላይት ለማምጠቅ አቅም ይፈጥርላታል'' ብለዋል።

ማዕከሉ የኢንዱስትሪና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ትስስር የሚያጠናክርም እንደሆነ ጠቅሰዋል።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም በበኩላቸው ለማዕከሉ ግንባታ የሚያስፈልገው የቅድመ ዝግጅት ስራ መከናወኑን አመልክተዋል።

ተማሪዎችም ከንድፈ ሀሳብ ያለፈ የተግባር እውቀት እንዲያገኙ አስተዋጽኦ ያደርጋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም