የቻይናዋ ውሃን ከተማ ነዋሪዎቻን መመርመር ጀመረች

64

አዲስ አበባ  ግንቦት 5/2012 (ኢዜአ) በዓለም ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ 19) የተቀሰቀሰባት የቻይናዋ ውሃን ከተማ የቫይረሱን በድጋሚ ማገርሸት ተከትሎ ሁሉንም የከተማዋን ናዋሪዎች መመርመር ጀምራለች።

የቻይና መንግሥት ትናንት በከተማዋ ያሉ ሁሉም አካባቢያዊ አስተዳደሮች በአስር ቀናት ውስጥ ምርመራውን አድርጎ ለማጠናቀቅ የሚያስፈልገውን ዝርዝር እንዲያቀርቡ ትዛዝ አስተላልፎ ነበር።

 ትዕዛዙ የተላለፈው የኮሮናቫይረስ መነሻ በሆነችው ዉሃን ከተማ ውስጥ ባለፈው ቅዳሜና እሁድ ስድስት ሰዎች ላይ ቫይረሱ ከተገኘባቸው በኋላ ነው።

ከዚህ በፊት ለአንድ ወር ያህል አንድም በሽታው ያለበት አዲስ ሰው ያልተገኘባት ውሃን፤ ቫይረሱ ዳግም እንዳያገረሽ ዛሬ ለከተማዋ ነዋሪዎች ምርመራ መጀመሩን ገልፍ ኒውስ በዘገባው አስነብቧል።

ዉሃን በወረርሽኙ ምክንያት ለአስራ አንድ ሳምንታት ጥብቅ በሆነ የእንቅስቃሴ ገደብ ውስጥ ቆይታ በሚያዝያ ወር ሁለተኛ ሳምንት ላይ ነበር የተከፈተችው።

በከተማዋ ለተወሰኑ ሳምንታትም ትምህርት ቤቶች ተከፍተው፣ የንግድ ተቋማት ሥራ ጀምረው እንዲሁም የሕዝብ መጓጓዣዎችም አገልግሎት መስጠት በመጀመራቸው ህይወት ወደ ነበረችበት መመለስ ጀምራ ነበር።

ቅዳሜና እሁድ ቫይረሱ በስድስት ሰዎች ላይ መከሰቱን ተከትሎ ከተማ እንቅስቃሴዋን ባታቆምም ነዋሪዎቹ በጥብቅ ጥንቃቄ የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴያቸውን ሲያከናውኑ ዘገባው በምስል አስደግፎ አቅርቧል።

ዛሬ ምርመራዋን የጀመረችው ዉሃን ሁሉንም የከተማዋን ነዋሪ ለመመርመር ባወጣችው ዕቅድ መሰረት ሁሉም የከተማዋ ከፍል በአስር ቀናት ውስጥ ምርመራው አድርጎ ለማጠናቀቅ የሚያስችለውን ዕቅድ ይዛለች።

ይሁን እንጂ ቢቢሲ ትናንት እንደዘገበው፤ የረጅም ጊዜ ልምድ ያላቸው በርካታ የጤና ባለሙያዎች የታቀደው ሁሉንም የከተማዋን ነዋሪ ለመመርመር የተያዘው ግዙፍ ዕቅድ ከፍተኛ ወጪን የሚጠይቅ ከመሆኑም በላይ አዋጪ እንዳልሆነ እየተናገሩ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም