ምርጫና የሰሞነኛው አጀንዳ …

61

አብዱራህማን  ናስር /ኢዜአ)

በአሁኑ ወቅት የመላው ዓለማችን ቀዳሚ መነጋገሪያ አጀንዳ የኮሮና ወረርሽኝ ወይም COVID-19 ሆኗል። መነሻውን ቻይና ውሃን ግዛት ያደረገው ይህ ወረርሽኝ በኢኮኖሚ የለጸጉ አገራትም ይሁን በማደግ ላይ ያሉ አገራት ላይ ከባድ ፈተናን ደቅኗል። የጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ መረጃ እንደሚያመለክተው  ደግሞ በዓለም በየቀኑ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በአማካይ ከ80 ሺህ በላይ ነው።

ወረርሽኙን ለመከላከልና የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ አገራት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጀዋል። ሰዎች ከቤታቸው እንዳይወጡ እገዳ ተጥሏል፣ የአምልኮ ቦታዎች፣ ት/ቤቶችና የንግድ ተቋማት ተዘግተዋል፣ የአየርና የየብስ ትራንስፖርቶች ተቋርጠዋል፤ በአጠቃላይ የእለት ተእለት እንቅስቃሴ ተገድቧል። ይህም ሆኖ እስካሁን የበሽታውን ስርጭት የሚገታው መፍትሔ ግን  አልተገኘም።

በአገራችን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከሰቱ ከተነገረበት መጋቢት ወር መጀመሪያ ሳምንት ጀምሮ እስከ  ግንቦት 4/2012 ዓ.ም ከ261 ሰዎች ቫይረሱ የተገኘባቸው ሲሆን እስካሁን 5 ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል። መንግስት ገና ከጅምሩ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የሰዎችን ግንኙነት የሚቀንሱ እርምጃዎችን መውሰድ የጀመረ ሲሆን፤ ቢሮ ገብተው መሥራ  ግድ ከሆኑት በስተቀር የመንግስት ሰራተኞች ከቤት ሆነው እንዲሰሩ፣ ት/ቤቶችና  የኃይማኖት ተቋማት ዝግ ሆነው እንዲቆዩ፣ ስብሰባ እንዳይካሄድ እንዲሁም የየብስና የአየር ትራንስፓርት ላይ ገደብ የሚጥሉ እርምጃዎች ተወስደዋል።

እስካሁን መፍትሔ ያልተገኘለት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በዓለም አቀፍ ደረጃ በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከፍተኛ ተጽእኖዎችን እያሳረፈ ነው። በአገራችንም በሁሉም መስክ ጫናዎችን አሳድሯል። ከእነዚህ መካከል አንዱና ዋነኛው በነሐሴ 2012 ዓ.ም በአገራችን ሊካሄድ ታቅዶ የነበረው አገር አቀፍ ምርጫ ነው።

ምርጫ በዜጎች ተሳትፎና እንቅስቃሴ እንዲሁም በበርካታ ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ እውን የሚሆን ሂደት ነው፡፡ የመራጮች ምዝገባን ጨምሮ የምርጫ ቅስቀሳ እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ ስራዎችን መስራትንም ይጠይቃል። በአሁኑ ወቅት በወረርሽኙ ሳቢያ አገራት ለምርጫ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ በከፍተኛ ሁኔታ ተስተጓጉሏል፡፡

በዚሁ ሥጋት የተነሳ በያዝነው ዓመት አገር አቀፍ፣ የአካባቢ እና የከተማ ምርጫ ለማካሄድ አቅደው የነበሩ ከ50 በላይ አገራት ጊዜውን ለማራዘም መገደዳቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ። ቦሊቪያ፣ ቺሊ፣ ስዊዘርላንድ፣ አውስትራሊያ፣ አርጀንቲና፣ ኬንያ፣ ኡጋንዳ፣ ደቡብ አፍሪካ የመሳሰሉት  ምርጫ ካራዘሙ አገራት መካከል ይጠቀሳሉ።  

የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድም በያዝነው ዓመት አገር አቀፍ ምርጫ ለማካሄድ የጊዜ ሰሌዳ አውጥቶ  ነሐሴ 23 ቀን 2012 ዓ.ም ምርጫ ለማካሄድ ዝግጅት ሲያደርግበት የነበረው ቢሆንም በአገሪቱ በተፈጠረው  የኮሮና ቫይረስ ወረሽኝ የተነሳ የታሰበውን ምርጫ ማካሄድ እንደማይቻል  አሳውቋል። በዚህ ምክንያት ምርጫ ማራዘም ይቻላል ወይስ አይቻልም? አሁን ያለው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የስልጣን ዘመን ሲያበቃ ቀጣይ ምን ሊሆን ይችላል? የተፈጠረውን ክፍተት በህጋዊ መንገድ እንዴት መፍታት ይቻላል? የሚሉና የመሳሰሉ ጥያቄዎች እንዲነሱ አድርጓል።

መንግስት በበኩሉ ምርጫው በተያዘለት ጊዜ ማካሄድ ካልተቻለ ለሚፈጠረው ክፍተት መፍትሔ ሊሆኑ የሚችሉ አራት አማራጮች ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እንዲካሄድበት አድርጓል። ይህን ተከትሎ የኢትዮጵያ ምርጫ ጉዳይ የሰሞነኛው የመነጋገሪያ አጀንዳ ሆኗል።

መንግስት ያቀረባቸው አራት አማራጮች

መንግስት በአገራችን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መስፋፋትን ተከትሎ ምርጫው በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ማካሄድ እንደማይቻል በምርጫ ቦርድ የቀረበውን መነሻ በማድረግ ጊዜውን ለማራዘም ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በማያፋልስ መልኩ ችግሩን ለመቅረፍ ያስችላሉ የተባሉ አራት አማራጮች አቅርቧል።  እንደ መፍትሔ አማራጮች የቀረቡት፡-

1. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን መበተን

2. የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ

3. ሕገ መንግሥት ማሻሻል

4. የሕገ መንግሥት ትርጓሜ መጠየቅ የሚሉት ላይ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ውይይት ተካሂዶበታል። ከተፎካከሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በተደረገ ውይይትም አብዛኛዎቹ የውይይቱ ተሳታፊዎች በህገ መንግስቱ መሰረት እስከ መጪው ነሐሴ ወር ማለቂያ ድረስ አጠቃላይ ምርጫ የማካሄድ ግዴታ ቢሆንም፣ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ምርጫውን ማከናወን ስለማያስችል ሕግና እውነታውን አጣጥሞ መሄድ አስፈላጊ ነው ሲሉ፤ ሌሎቹ ደግሞ መፍትሔው ፖለቲካዊ ነው የሚል ሃሳብ አቅርበዋል።     

የፖለቲካ ፓርቲዎች አቋም

መንግስት አራት አማራጮች ማቅረቡን ተከትሎ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉዳዩን በማስመልከት ያወጧቸው መግለጫዎች  የተለያዩ  አቋሞች የተንጸባረቁበት ነበር። የፓርቲዎቹ መግለጫዎች በጥቅሉ በሁለት ተከፍለው ሊታዩ የሚችሉ ናቸው።

  1. ፖለቲካዊ መፍትሔ

ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ኦፌኮ፣ ኦነግ፣ ኦብነግ፣ አብሮነትና  አረና  በህገ መንግስቱ ምርጫን ስለማራዘም የተቀመጠ ነገር ስለሌለ መፍትሔው ህጋዊ ሳይሆን ፖለቲካዊ መሆን አለበት የሚል  አቋም አላቸው።

አቋሙን  የሚያራምዱት እነዚህ  የፖለቲካ ፓርቲዎች  በመንግስት የቀረቡት አራቱ አማራጮች ህጋዊ መሰረት የላቸውም ይላሉ። ፓርቲዎቹ በኢፌዴሪ ህገ-መንግስት ምርጫን ለማራዘም ተብሎ የተቀመጠ አንድም አንቀጽ ባለመኖሩ በአሁኑ ወቅት በአገራችን ህገ-መንግስታዊ ቀውስ ተፈጥሯል የሚል እምነት እንዳላቸው በመግለጽ ለችግሩ መፍትሄ መስጠት የሚቻለው በመደበኛ የህግ አሰራር ሳይሆን ከመደበኛ የህግ አሰራር ውጭ በሆነ መንገድ ነው ብለው ያብራራሉ።

ህገ መንግስቱ ምርጫ በየ5 ዓመቱ መካሄድ እንዳለበት በግልጽ ስላስቀመጠ ትርጉም የሚያስፈልገው አሻሚ ነገር የለም ሲሉም ይሞግታሉ። በመሆኑም የቀረቡት አራቱ አማራጮች ስልጣን ለማራዘም ተብሎ የቀረቡ ናቸው ሲሉ የቀረቡትን  አማራጮች  እንደማይቀበሏቸው ይገልጻሉ።

ይህን አስተሳሰብ የሚያራምዱ ፓርቲዎች አንዳንዶቹ ምርጫው ህገ መንግስቱ ባስቀመጠው የጊዜ ገደብ ይካሄድ፤ ይህ ካልሆነ ችግር ያጋጥመናል የሚሉ ሲሆን፤ ሌሎቹ ደግሞ የወቅቱ ሁኔታ ምርጫ ለማካሄድ እንደማያስችል በማመን፤ ነገር ግን ህጋዊ መንገድ ዝግ ስለሆነ ድርድር ይደረግ የሚሉ ናቸው። ፓርቲዎቹ ከመስከረም 30 ቀን 2013 ዓ.ም በኋላ በህጋዊ መንገድ የተመረጠ መንግስት ስለማይኖር በፖለቲካ ፓርቲዎች ድርድር ላይ የተመሰረተ የሽግግር መንግሥት ሀገሪቱን ሊመራ ይገባል ሲሉ ተደምጠዋል።

  • ህገ መንግስታዊ መፍትሔ

አሁን የተፈጠረው ሕገ መንግሥታዊ ክፍተት በሕገ መንግስታዊ አግባብ ሊፈታ ይችላል የሚል  አቋም የሚያራምዱት ደግሞ  ኢዜማ፣ ነፃነትና እኩልነት፣ አብንና  ብልጽግና ናቸው።

ይህን አቋም የሚያራምዱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚወሰዱ ማንኛውም አማራጮች አሁን ያለንበትን አስቸጋሪ እና ፈታኝ ወቅት ከግምት ያስገቡ፣ የሀገር መረጋጋት፣ ሰለም እና ቀጣይነትን የሚያረጋግጡ፣ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሂደቱን የሚያስቀጥሉ እንዲሁም አሁን ከገባንበት ሕገ መንግሥታዊ አጣብቂኝ በአስተማማኝ ሁኔታ የሚያስወጡን መሆን አለባቸው የሚል እምነት እንዳላቸው ይገልጻሉ። ምርጫው እንዲራዘም ህገ መንግሰታዊ መሰረት ያለው መፍትሔ መከተል ለአገሪቱ ዘላቂ መፍትሔ የሚያመጣ፣ ሀገረ መንግስቱን የሚያስቀጥልና ወደ ተረጋጋ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የሚደረገውን ሽግግር የሚያግዝ ነው ሲሉም አቋማቸውን ያጠናክራሉ።

ፓርቲዎች እንደ መፍትሔ የሚያቀርቧቸው አማራጮች ሁለት ናቸው። አንዳንዶቹ በህገ መንግስቱ አንቀጽ 105/2 ሀ እና ለ አሰራር መሠረት ስለምርጫ የሚደነግገውን አንቀጽ 58/3 ማሻሻል ይገባል ሲሉ ሌሎች ደግሞ በተወሰኑ አንቀጾች ላይ በሚመለከተው አካል የህገ መንግስት ትርጉም እንዲሰጠው ይጠይቃሉ።          

ህገመንግስታዊ ትርጉም ይሰጠው የሚሉት ፓርቲዎች፤ የሚያስፈልገን የፖለቲካ መፍትሔ ነው ብለው የሚሞግቱ ፓርቲዎች ያቀረቡትን የሽግግር መንግስት መመስረት አለበት የሚል አስተሳሰብ አይቀበሉም። ለዚህም በምክንያትነት የሚጠቅሱት ሀገር አቀፍም ሆኑ የክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የመደማማጥ፣ የመረዳዳት እና አብሮ የመስራት ታሪክ የሚጎድላቸው በመሆኑ በጋራ የሽግግር መንግስት መስርተው አገር ሊመሩና ወደ ዴሞክራሲ ሊያሻግሩ አይችሉም የሚል ነው። አሁን ያሉትን የፖለቲካ ፓርቲዎች የእርስ በርስ ግንኙነት እና የቁጥር ብዛት ከግምት ያላስገባ በመሆኑ ተግባራዊ ሊደረግ የማይችል ከመሆኑ በተጨማሪ ጠንካራ የመንግሥት መዋቅር የማይፈጥር፤ ችግሩን ከመፍታት ይልቅ ወደ ባሰ ሀገራዊ ቀውስ ሊከተን የሚችል ነው ሲሉም ይሞግታሉ። 

የምሁራንና የህግ ባለሙያዎች አስተያየት

ምርጫውን በማራዘም ሂደት ሊያጋጥሙ የሚችሉትን ህገመንግስታዊ ጉዳዮች በተመለከተ ምሁራንና የህግ ባለሙያዎች የራሳቸውን አስተያየት ሰንዝረዋል። ምሁራኑ በርካታ የዓለም አገራት በተከሰተው ወረርሽኝ ምክንያት ምርጫ ለማራዘም መገደዳቸውን በማንሳት ኢትዮጵያም ከነባራዊ ሁኔታ ውጪ ልትሆን እንደማትችል ያስረዳሉ። ከማንኛውም አጀንዳ ቅድሚያ ለህዝብ ህልውና መቆም እንደሚገባ በመግለጽ አሁን ሀገሪቱን የገጠማትን ፈተና ለመወጣት በሰከነ መንገድ ማሰብ እንደሚጠይቅም ይገልጻሉ።

በቅርቡ ኢዜአ ያነጋገራቸው የተለያዩ ዩኒቨርሲቲ ምሁራንና የህግ ባለሙያዎች መንግስት ያቀረባቸው አራቱም አማራጮች ህገ-መንግስታዊ መሰረት ያላቸው ናቸው ይላሉ። ባለሙያዎቹ አሁን አገሪቱ ከገጠማት ችግርና አገራዊ ሁኔታ አንጻር ግን ህገ መንግስት መተርጎም የተሻለ አማራጭ ነው የሚል እምነት አላቸው።

የኢፌዴሪ ህገ መንግስት ምርጫ በየ 5 ዓመቱ እንደሚካሄድ የደነገገ መሆኑን የሚገልጹት የህግ ባለሙያዎች አሁን የተፈጠረው ዓይነት ክስተት ሲያጋጥም በአንቀጽ 58 ንኡስ ቁጥር 3 ምርጫ ሳይካሄድ ቢቀር እንደሌሎች አገራት መፍትሔ በግልጽ ባለማስቀመጡ ትርጉም ይፈልጋል ይላሉ። ባለሙያዎቹ እንደሚገልጹት ህገ መንግስቱ ክፍተቱን ለመሙላት ራሱ ክፍት አድርጎ ስለማይተወው መሻሻልና መዳበር በሚችልበት ሁኔታ ላይ የሚሰራ ነው ባይ ናቸው።

በህገ መንግስት አጣሪ ጉባኤ አሰራር አዋጅ ቁጥር 798/2005 አንቀጽ 3 ሥር የፌዴራል ወይም የክልል ም/ቤት አባላት የህገመንግስት ትርጉም ጥያቄ ሊያቀርቡ እንደሚችሉና ሀሳቡ በ1/3ኛ አባላት ከተደገፈ ተቀባይነት እንደሚኖረው ይደነግጋል ሲሉ ይናገራሉ።

በመሆኑም አገሪቱ በአንድ በኩል በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ መሆኗን በሌላ በኩል የፓርላማ ማብቂያ ጊዜ በመድረሱ ሁለቱ ጉዳዮች እንዴት ተጣጥመው መቀጠል ይችላሉ? የሚለው ጉዳይ ግልጽ የሆነ መፍትሔ ይፈልጋል ሲሉም ያብራራሉ። ህገ መንግስት አንዴ ያለቀና አይነኬ አይደለም የሚሉት እነዚህ የህግ ባለሙያዎች በየደረጃው ያሉ የአገርን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘቡ ማሻሻያዎችን ማስተናገድ መቻሉ ዴሞክራሲን የመለማመድ ምልክት መሆኑን በመግለጽ ህገ መንግስት መተርጎም የሚለውን የመፍትሔ ሃሳብ ይደግፋሉ።   

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውሳኔ

በኮሮና ቫይረስ ወረሽኝ ምክንያት የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ በህገ-መንግስቱ በተቀመጠው መሰረት አጠቃላይ ምርጫውን ማድረግ የማይችል መሆኑን በመግለጽ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውሳኔ እንዲያሳልፍ  ባቀረበው ጥያቄ መሰረት ምክር ቤቱ ሚያዝያ 22 ቀን 2012 ዓ.ም በአራቱ አማራጭ የመፍትሔ ሃሳቦች ዙሪያ ውይይት አካሂዷል። በውይይቱ ወቅትም  የተለያዩ ሃሳቦች ተንሸራሽረዋል።

አብዛኞቹ የምክር ቤት አባላት በወረርሽኙ ምክንያት ቦርዱ ምርጫ ማካሄድ እንደማይችል መግለጹ ተገቢ ነው ብለው ያምናሉ። ምክር ቤቱም በሽታው ወረርሽኝ መሆኑን በማመን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጁን በመጥቀስ በመንግስት ከቀረቡ አራት አማራጮች ውስጥ የህገ መንግስት ትርጉም መጠየቅ የሚለውን በአማራጭ መፍትሔነት በመቀበል ውሳኔ አሳልፏል። በዚህ ውሳኔ መሰረት ከአንድ ወር ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ የህግ ትርጓሜ የሚሰጣቸው የህገ መንግስቱ አንቀፆች አንቀፅ 54/1፣ 58/3 እና 93 ናቸው።

ይህን ውሳኔ ተከትሎ የሕገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ከምክር ቤቱ በቀረበለት የሕገ መንግስት ትርጉም ጥያቄ ላይ ተወያይቶ ውሳኔ ወይም የውሳኔ ሃሳብ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ለማቅረብ ያስችለው ዘንድ የሚመለከታቸው ተቋማት እና የህግ ባለሙያዎች የሙያ አስተያየት እንዲያቀርቡ ጥሪ አድርጓል። የሂደቱን እና የውጤቱን ተዓማኒነት እንደሚያሳድገውና የህገ መንግስታዊ ስርዓት ባህል እንዲዳብር እንደሚረዳ ብዙዎች ይስማማሉ።

ከፖለቲካም ሆነ ከማንኛው ጉዳይ በፊት የህዝብ ጤናና ደህንነት ይቀድማልና የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ መንግስት እንዲሁም ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የኮሮና ሻይረስ ስርጭትን  ለመግታት በጋራ መንቀሳቀስ ይገባል። የሚካሄደው ምርጫም ውጤታማ ሆኖ አገርን መምራት የሚቻለው ህዝብ ሲኖር ነውና  ለዜጎች ደህንነት ቅድሚያ መስጠት ይገባል እንላለን።   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም