ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት የሰዎች ሞት በሁለት እጥፍ ሊጨምር ይችላል

75

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 4/2012 (ኢዜአ) ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት በኮቪድ 19 እና በተዛማጅ የኤች አይ ቪ ቫይረስ ሳቢያ የሰዎች ሞት በሁለት እጥፍ ሊጨምር እንደሚችል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተ.መ.ድ) አስታወቀ።

ድርጅቱ ለኤች.አይ.ቪ ታማሚዎች የሚደረገው የጤና አጠባበቅ የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ተከትሎ የሚቀዛቀዝ ከሆነ 500 ሺህ የሚጠጉ ታማሚዎች ህይወት ሊያልፍ እንደሚችል አስጠንቅቋል።

በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ሳቢያ ለኤች.አይ.ቪ ታማሚዎች የሚሰጠው ህክምና ለ6 ወራት ከተስተጓጎለ እኤአ በ2020 እና 2021 ብቻ ተጨማሪ 500 ሺህ ሰዎች ህይወታቸውን ሊያጡ እንደሚችሉ የዓለም ጤና ድርጅትና የተባበሩት መንግስታት በጋራ ባወጡት መግለጫ አመልክተዋል።

እኤአ በ2018 ብቻ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት ኤች አይ ቪ ኤድስ ጋር ተያያዥ በሆኑ በሽታዎች 470 ሺህ ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል።

የኤች.አይ.ቪ ህክምና አገልግሎት ከተዘጋ ፣ የህክምና አቅርቦት ሰንሰለቱ ከተቋረጠ ወይም የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ተከትሎ የጤና አጠባበቅ አገልግሎቱ ከተስተጓጎለ ጉዳቱ የከፋ ይሆናል ሲሉ ሁለቱ የመንግስታቱ ድርጅት አካላት አስጠንቅቀዋል።

የዳሰሳ ምልከታው እንደጠቆመው የኤች.አይ.ቪ ጤና አጠባበቅ አገልግሎት ለ6 ወራት ከተቋረጠ እኤአ በ2008 በአህጉሪቱ በኤድስ ምክንያት ህይወታቸው ካለፈው 950 ሺህ ሰዎች ጋር የሚስተካከል ጉዳት ሊያደርስ ይችላል ተብሏል።

"በአፍሪካ ከኤች አይ ቪ ጋር በተያያዘ ተጨማሪ 500 ሺህ ሰዎች ይሞታሉ የሚለው ግምት እጅግ አስደንጋጭ ከመሆኑ ባለፈ ወደ ቀደመው ታሪክ መመለስን የሚያሳይ ነው” በማለት የአለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ተናግረዋል።

"አገራት የቀረበውን ጥሪ የማንቂያ ደወል አድርገው በመውሰድ ሁለንተናዊ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማሳደግ መስራት አለባቸው”ብለዋል ዋና ዳይሬክተሩ።

ይህ ካልሆነ ግን በቀጣዩ አምስት ዓመታት በርካታ ሰዎች ህይወታቸውን ያጣሉ በማለት የተባበሩት መንግስታት አሳስቧል።

እኤአ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት 25 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሰዎች የኤች.አይ.ቪ ቫይረስ ያለባቸው ሲሆን 16 ነጥብ 4 ሚሊዮኑ ደግሞ የዕድሜ ማራዘሚያ መድሃኒት ይወስዳሉ።

"ዓለም አቀፍ ተቋማት የመመርመሪያና የህክምና መስጫ መሳሪያዎች በእጅጉ ለሚያስፈልጋቸው አገራት አቅርቦታቸውን እንደሚቀጥሉ እርግጠኛ ነን በማለት”ዶክተር ቴዎድሮስ ተስፋ አድርገዋል።

በጥናቱ መሰረት የስድስት ወራት መስተጓጎል ብቻውን በአንድ ዓመት ከኤች አይ ቪ ጋር በተያያዘ በተጨማሪ የሚሞቱ ሰዎቸን ቁጥር ከ471 ሺህ አስከ 673 ሺህ ሊጨምር ይችላል።

የአገልግሎቱ መቋረጥ ኤች.አይ.ቪ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ በማድረግ የተገኘውን ስኬት ወደ ኋላ ሊመልሰው እንደሚችልም ተሰግቷል።

ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት በኤች.አይ.ቪ የሚያዙ ህፃናት ቁጥር እኤአ በ2010 ከነበረበት 250 ሺህ በ2018 ወደ 140 ሺህ ወይም በ43 በመቶ መቀነሱ አይዘነጋም።

ለእናቶችና ለህፃናት የሚሰጠው የኤች.አይ.ቪ አገልግሎት በመቀዛቀዙ ምክንያት የኤች.አይ.ቪ ኢንፌክሽን በሞዛምቢክ 37 በመቶ፣ በማላዊ እና ዚምባቡዌ 78 በመቶ፣ በዑጋንዳ ደግሞ 104 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ሞዴል ጥናቱ ማመላከቱ ተገልጿል።

"ለኤች አይ ቪ ቫይረስ ምላሽ ለመስጠት በተደረገው ትንቅንቅ የተገኘው ውጤት ኮቪድ 19ን ለመዋጋት በተያዘው ግብግብ መስዋዕት ሆኗል” በማለት የመንግስታቱ ድርጅት የኤች አይ ቪ ኤድስ ምላሽ ዋና ዳይሬክተር ዊኒ ባያናዬማ ተናግረዋል።

"ዝም ብለን እጃችንን አጣምረን ተቀምጠን በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ በተለይ ደግሞ ወጣቶች በግዴለሽነት ህይወታቸውን እንዲያጡ መፍቀድ የለብንም።

መንግስታት ከኤች.አይ.ቪ ጋር ለሚኖሩ በመደበኛነት የእድሜ ማራዘሚያ መድሃኒት እንዲያቀርቡ በፅኑ አሳስባለሁ፤ በቀላል አገላለጽ አቅርቦቱ ለእነሱ የህይወት አድን ነው ።" በማለት ባያናዬማ ተናግረዋል።

ኤች.አይ.ቪ  ከተከሰተበት ቀን አንስቶ ባለፉት 35 ዓመታት 78 ሚሊዮን ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ 35 ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ በኤች አይ ቪ እና ተጓዳኝ በሽታዎች ህይወታቸው ማለፉን የመንግስታቱ ድርጅት መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም