ሰራተኛው መብቱን ለማስጠበቅ ተደራጅቶ መንቀሳቀስ አለበት---ዶክተር ሂሩት ወልደ ማሪያም

94
ባህር ዳር ሰኔ 28/2010 ሰራተኛው መብቱን ለማስጠበቅና ህገ ወጥ አሰሪዎችን በህግ ተጠያቂ ለማድረግ ተደራጅቶ መንቀሳቀስ እንዳለበት የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ወልደ ማሪያም አሳሰቡ። "በስራ ቦታዎች ማህበራዊ ምክክርን በማሳደግ ምቹ የስራ ሁኔታ እንፍጠር"  በሚል መሪ ሃሳብ የአማራ ከልል አሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ  ቢሮ ከባለድርሻ አካላት ጋር በባህር ዳር ከተማ እየተወያየ ነው። በውይይት መድረኩ የተገኙት ሚኒስትሯ እንዳሉት ሰራተኞች በአሰሪዎች የሚደርስባቸውን አላስፈላጊ የጉልበት ብዝበዛ ለመከላከል በተናጥል የማይቻል ነው፡፡ ተደማጪነትም ለማግኘትና መብትን ለማስጠበቅ አማራጩ ሰራተኛው ተደራጅቶ መንቀሳቀስ እንዳለባት አሳስበው በዚህም የሚያቀርባቸውን ማናቸውም ቅሬታዎች መንግስት ተከታትሎ እርምጃ ለመውሰድ ቁርጠኛ መሆኑን አስታውቀዋል። አሁን በስራ ላይ ያለው የአሰሪና ሰራተኛ ህግ የሰራተኛውን መብት ለማስጠበቅና ለሰላማዊ የኢንዱስትሪ እንቅስቃሴ ውስንነት ያለበት መሆኑ ታምኖበት ለማሻሻል እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። የሰራተኛውን ተደራጅቶ የመንቀሳቀስ መብት የማይቀበሉ አሰሪ ተቋማት እንዳሉ የገለጹት  ደግሞ የአማራ ክልል ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ዶከተር ሞላ ጀንበሬ ናቸው። "በክልሉ 309 የሰራተኛ ማህበራት ያሉ ቢሆንም የሰራተኞቻቸውን ጥቅም ለማስከበር ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ከአሰሪዎቻቸው ጋር የውል ስምምነት ያሏቸው 43ቱ ብቻ ናቸው "ብለዋል። ቢሮው የሰራተኞችን መብት ለማስጠበቅ ጥረት ቢያደርግም  ሰራተኞቹ ተደራጀተው መብቶቻቸውን ሊጠይቁ ባለመቻላቸው ችግሮች አሁንም እንደቀጠሉ ናቸው። በዚህም ምክንያት በተያዘው ዓመት ብቻ ከ600 በላይ ሰራተኞች በስራ ላይ ጉዳት እንደደረሰባቸው አመልክተዋል። በውይይቱ የተሳተፉ ሰራተኞችም  ለሰሩበት ተገቢውን ዋጋ እየተከፈላቸው እንዳልሆነና አስፈላጊ ጥቅማጥቅሞችም እየተከበሩላቸው እንዳልሆነም ጠቁመዋል። ከቡሬ ከተማ ውሃ አገልግሎት የመጡት አቶ ዋለልኝ መኩሪያ በበኩላቸው ለሚሰራው የትርፍ ሰዓት ክፍያና ጥቅማጥቅሞች የማይሟሉ ካሉ የሰራተኛው ተገቢ  ጥያቄ በመሆኑ መስተካከል እንዳለበት አመልክተዋል። ለሰራተኛው ለሰራበት ተገቢውን ክፍያ እየተከፈለው እንዳልሆነ የተናገሩት ደግሞ  ከጎንደር ጎሀ ሆቴል የሰራተኛ ተወካይ ሆነው የውይይቱ ተሳታፊ አቶ  ተቀባ አክሊሉ ናቸው። ሰራተኛው ተደራጅቶ ቢጠይቅም ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት አሰሪው ፍቃደኛ እንዳለሆነም ጠቁመዋል። ለሁለት ቀን በሚቆየው የውይይት መድረኩ የተለያዩ ድርጅቶች ሰራተኛ ተወካዮች፣ የፌደራልና የክልል የስራ ኃላፊዎች እየተሳተፉ ሲሆን አሰራዎች ግን እንዳልተገኙ ነው ሪፖርተራችን ከስፍራው የዘገበው፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም