የከፋ የጤና መታወክ እንዳይፈጠር መደበኛ የህክምና አገልግሎትን መከታተል ይገባል … ጤና ባለሙያዎችና ታካሚዎች

53

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 02/2012 (ኢዜአ) የኮሮና ቫይረስ መከሰትን ተከትሎ በህብረተሰቡ የተፈጠረው ስጋትና መደናገጥ ወደ ጤና ተቋማት መሄድ ቀንሶ የነበረ ቢሆንም፤ እየተሰጡ ባሉ የግንዛቤ  ማስጨበጫ የተገልጋዮች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሆኑን የጤና ባለሙያዎችና አንዳንድ ተገልጋዮች ገለጹ፡፡

ከኮሮና ቫይረስ ባሻገርም ህይወትን ሊቀጥፉ የሚችሉ በሽታዎች በመኖራቸው በየካቲት 12 ሆስፒታል ከኮሮና ምርመራ ጎን ለጎን መደበኛ የህክምና አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን  የሆስፒታሉ ሜዲካል ኮሌጅ ዋና ፕሮቮስት ዶክተር አየለ ተሾመ ገልጸዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ  የማይጨው ጤና ጣቢያ ለህክምና መሄዳቸውን የገለፁት ወይዘሮ ሰናይት ሙላቱ  በበኩላቸው፤ የኮሮና ቫይረስ ኢትዮጵያ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ ወደ ህክምና ተቋም መሄድ ስጋት እንደፈጠረባቸው ይናገራሉ፡፡

ከአሁን በፊት ራሳቸውም ሆነ ቤተሰባቸው ሲታመሙ በፍጥነት ወደ ጤና ተቋም የመሄድ ልምድ እንደነበራቸው ጠቅሰው፤ በወረርሽኙ ስጋት ወደ ጤና ተቋም መሄድ  አቁመው እንደነበረና አሁን ህመም ሲብስባቸው መሄዳቸውን ነው የገለጹት።  

ወደ ጤና ተቋም ከሄዱ በኃላ ግን ያስተዋሉት ጥንቃቄ የተሞላው የአገልግሎት አሰጣጥ ስጋታቸውን እንደቀነሰላቸውና  ህብረተሰቡ ለባሰ የጤና ቀውስ ሳይዳረግ ህክምና ማግኘት እንዳለበትም አንስተዋል፡፡

ሌላዋ ለእርግዝና ክትትል በቤተሰብ ግፊት የመጣች  መሆኑን  የተናገረችው ወይዘሮ መሰረት ታምሩ፤ ቫይረሱን በመፍራት በቤት ውስጥ ለመውለድ ወስና ነበር።  

ነገር ግን ጤና ጣቢያ ስትሄድ ባስተዋለችው ጥንቃቄ ሌሎች እናቶችም በቤት ውስጥ ሲወልዱ ሊደርስባቸው የሚችለውን አደጋ ለመቀነስ  በህክምና ተቋም መውለድ እንዳለባቸው መክራለች፡፡

የማይጨው ጤና ጣቢያ ሜዲካል ዳይሬክተር  ዶክተር  ባለ ስራው፤ ተገልጋዮች በወረርሽኙ እንዳይጠቁ ተቋማቸው ከበፊቱ በተሻለ ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ  አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ተቋሙ በርካታ ተገልጋይ ያለው ቢሆንም በወረርሽኙ አመካኝነት ቁጥሩ እየቀነሰ መሄዱን  ገልፀው፤ አሁን እየተሰጠ ባለው የግንዛቤ ማስጨበጫ አገልግሎቱ  እየጨመረ ነው፡፡

ከቅዱስ ጴጥሮስ ወደ ጤና ጣቢያው የሚላኩ እናቶችና ህፃናት ባለሙያና አስፈላጊ ቁሳቁስ አብሮ በመመደቡ የክትትልና የማዋለድ ስራ ላይ ብዙም ጯና እንዳልፈጠረባቸውም ጠቅሰዋል። 

እናቶች  በወረርሽኙ ስጋት በቤት ውስጥ ለመውለድ እንዳይገደዱ የጤና ባለሙያዎች ቤት ለቤት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ እየሰሩ መሆኑን የገለጹት ዶክተር  ባለ፤ ህብረተሰቡ በፍራቻ  ለከፋ የጤና ቀውስ እንዳይዳረግ የሚዲያ ተቋማትም የግንዛቤ ስራዎችን መስራት  አለባቸው  ነው ያሉት።

በየካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ ዋና ፕሮቮስት ዶክተር አየለ ተሾመ በበኩላቸው፤ በሆስፒታሉ፤ ከኮሮና ቫይረስ ምርመራ ጎን ለጎን መደበኛ የህክምና አገልግሎትም እየተሰጠ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ተቋሙ የወረርሽኙን  ስርጭት ለመግታት አገልግሎት ፈልገው ለሚሄዱ ሰዎች በር ላይ ሙቀታቸውን በመለካት አጠራጣሪ ምልክቶች ካሳዩ ተጨማሪ ምርመራ በማድረግ ውጤት እስኪደርስ ወደ ለይቶ ማቆያ እንዲገቡ ይደረጋል ብለዋል፡፡

ሆስፒታሉ የነበረውን የሰው ብዛት ለመቀነስ ታማሚዎችን ለመጠየቅ የሚመጡ ሰዎችን ማስተናገድ ያቆመ ሲሆን፤ ተኝተው ለሚታከሙ አንድ አስታማሚ ብቻ ነው የሚፈቀደው።

ወረርሽኙ አለም አቀፍ በመሆኑ የህክምና ቁሳቁሶችን ማግኘት ሊያዳግት እንደሚችል ጠቅሰው፤  ግብአቶችን ለመቆጠብ አንዳንድ  ድንገተኛ ያልሁኑ የቀዶ ጥገና ህክምናዎችን አራዝመናል ብለዋል።

እንደ እንቅርት፣ የሃሞት ጠጠርና የሌሎች ግዜ የሚሰጡ ህመሞች ከ2 እና 3 ወር በኃላ ቀዶ ጥገና ቢሰራም በጤና ላይ ሊፈጥር የሚችለው ችግር እንደሌለም ዶክተር  አየለ ገልጸዋል።

ጊዜ የማይሰጡና ገዳይ የሆኑ በሽታዎችን ደግሞ ሆስፒታሉ  ከኮሮና ምርመራ ጎን ለጎን መደበኛ የህክምና አገልግሎት እየሰጠ ነው ብለዋል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከክልል የሚመጣውን የትራንስፖርት ፍሰት እንዲቀንስ በማድረጉ ከርቀት ለሚመጡ ታካሚዎች  አስቸጋሪ ሆኖ የቆየ ቢሆንም፤ መንገድ በመከፈቱ ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ እየመጡ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

ተቋሙ ከወረርሽኙ ጋር ተያይዞ የልየታ ስራ፣ ሰዎች የከፋ ህመም ላይ ሆነው  የኮሮና እንዳለባቸው የሚጠረጠሩ ከሆነ ተኝተው አገልግሎት እንዲያገኙ እያደረገ ሲሆን፤ በ6ኪሎ፣4ኪሎና 5ኪሎ ዩኒቨርሲቲ ለይቶ ማቆያ የሚገኙና ከአረብ ሃገራት የመጡ ሰዎችን የመከታተል ሃላፊነት እንዳለበትም  ገልፀዋል፡፡

የጤና ሚኒስቴር ከኮሮና ቫይረስ ባሻገር ህብረተሰቡ የህመም ስሜት ሲኖረው ተገቢውን ጥንቃቄ በመውሰድ ወደ ጤና ተቋማት በመሄድ መደበኛ አገልግሎቶት ማግኘት እንደሚችል በተለያዩ ሚዲያዎች እየገለፀ መሆኑን ጠቅሰው፤ ሁሉም የሚዲያ ተቋማት የድርሻቸውን በመወጣት እገዛ እንዲያድርጉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም