አርሶ አደሮች ለሚያከናውኑት የዘመነ ግብርና የክልሉ መንግስት ከጎናቸው ነው

112

ነቀምቴ ኢዜአ ግንቦት 1/2012 የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ወደ ኢንቨስትመንት የተሸጋገሩት አርሶ አደሮች ግብርናን አዘምነው እንዲሰሩ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ።

በክልል ደረጃ በአምስት ክላስተር ላይ የተካሄደው የኦሮሚያ ኢንቨስትመንት ቀን የእውቅና ስነ ስርዓት   በነቀምቴ ከተማ ተካሄዷል።

በእውቅና ስነስርዓቱ ላይ የተገኙት በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የገጠር ክላስተር አስተባባሪ ዶክተር ግርማ አመንቴ እንዳሉት ዛሬ ወደ ኢንቨስተርነት የተሸጋገሩት አርሶ አደሮች "የዝናብ ውሃን ሳይጠብቁ በመስኖ እርሻ በዓመት ሁለትና ሶስት ጊዜ ማምረት ይጠበቅባቸዋል"።

ከአርሶ አደርነት ወደ ኢንቨስተርነት ባደረጉት ሽግግር ላይ ያልተለያቸው የክልሉ መንግስት ድጋፍ ለወደፊቱ ተጠናክሮ ይቀጥላል ያሉት ዶክተር ግርማ  የክልሉ መንግስትም የውሃ መሳቢያ ሞተሮችን፣ ትራክተሮችን እንዲሁም ኮምባይነሮችን ከቀረጥ ነጻ አስገብቶ በተመጣጣኝ ዋጋ እያከፋፈለ መሆኑን በማሳያነት አውስተዋል።

በኢንቨስተርነት የሚሰሩባቸው መሬቶችም ከሊዝና ኪራይ ነጻ እንደተደረገላቸው የገለጹት አስተባባሪው ለዚህም "እንኳን ደስ አላችሁ" ብሎአቸዋል።

ዶክተር ግርማ አክለውም ዛሬ የተሸጋገራችሁ አርሶ አደሮች ግብርናን ከማዘመን ጎን ለጎን የግብርና ኢንዱስትሪ ትስስሩን በማጠናከር ለዜጎች ሰፊ የስራ እድል መፍጠር አለባችሁ ብለዋል።

ወደ ኢንቨስትመንት የተሸጋገሩት አርሶ አደሮች በበኩላቸው "መንግስት ባመቻቸልን መስክ ወደ ኢንቨስተርነት በመሸጋገራችን የተሰማንን ደስታ እየገለጽን ለወደፊቱም የበለጠ ሰርተን አገራችንን ለመለወጥ መነሳሳትን ፈጥሮልናል" ሲሉ ተናግረዋል ።

በነቀምቴ ከተማ በተካሄደው የእውቅና ስነስርዓት ላይ 122 የምስራቅ፣  ምእራብና ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞኖች አርሶአደሮችና 9 ጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ወደ ኢንቨስተርነት እንዲሸጋገሩ ተደርጓል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም