በዚህ ዓመት መጠናቀቅ የነበረበት የአበበ ቢቂላ ስታዴየም ጥገና ከግማሽ አልዘለለም

1195

አዲስ አበባ ሰኔ 27/2010 በዚህ ዓመት መጠናቀቅ የነበረበት የአበበ ቢቂላ ስታዴየም የእድሳትና ጥግና እንዲሁም ዙሪያ ሼድ ግንባታ 48 በመቶው ብቻ መጠናቀቁ ተገለጸ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ሴቶችና ህጻናት ቋሚ ኮሚቴ፣ ጋዜጠኞችና  የቢሮው ሰራተኞች በተገኙበት በከተማዋ  እየተገነቡ የሚገኙ  ትላልቅ የስፖርት የግንባታዎችን አስጎብኝቷል።

የመስክ ጉብኝት ከተደረገባቸው ቦታዎች መካከል የአበበ ቢቂላ ስታዴየም ጥገናና ዙሪያ ሼድ ስራ፣ የአቃቂ ቃሊቲ ስታዴየም ግንባታና የራስ ኃይሉ መዋኛ ገንዳ ግንባታ ስራዎች ናቸው።

በጉብኝቱም የአበበ ቢቂላ ስታዴየም የጥገናና እድሳት እንዲሁም ዙሪያ ሼድ ስራ በዚህ ዓመት መጠናቅቀ የነበረበት ቢሆንም 48 በመቶው ብቻ መጠናቀቁ እንደ ጉድለት ተነስቷል።

የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ የአበበ ቢቂላ ስታዲየም ለማከናወን በ105 ሚሊዮን ብር ወጪ የዙሪያው የጣሪያ ማልበስና የወንበር ተከላ እንዲሁም ሌሎች የእድሳት ስራዎችን ለማከናወን ባለፈው ዓመት የካቲት ወር ላይ ጫረታውን ካሸነፈው የቻይናው ኩባንያ ዥዋንግሚ ኢንጂነሪንግ ጋር የውል ስምምነት የተፈራረመው።

ስታዲየሙን በ18 ወራት ለመጠናቀቅ እቅድ ተይዞለት የነበረ ሲሆን፤ ስራው ግን ከግማሽ አልዘለለም።

ለዚህም በዋና ምክያትንት የተቀመጠው  ብዙ እቃዎች ከውጭ የሚገቡ በመሆናቸው ቶሎ አለመድረስ እንደትልቅ ችግር ተነስቷል።

ከዚህ በተጨማሪ  የመብራት ኃይል አቅርቦት በቂ አለመሆንም ግንበታው በሚከናወንበት ቦታ የሚሰሩ የጣሪያ ተሸካሚ ብረቶችን ለመስራት በመቸገራቸው እንደሆነ ነው የተገለጸው።

የክረምቱ ጊዜም ከሚጠበቀው ጊዜ ፈጥኖ መግባቱ ለስታዲየሙ ስራ የራሱን ተጽእኖ አድርጓል ተብሏል።

እስካሁንም በስታዲየሙ ዙሪያ ያሉ ሱቆች ጥገና፣ የተጫዋቾች የልብስ መቀየሪያ ቦታና  መጸዳጃ ቤት ስራዎች በመጠናቀቅ ላይ ናቸው ተብሏል።

የአበበ በቂላ ስታዲየም የጣሪያ ማልበስ፣ ወንበር ተከላና የመሮጫ ትራክ ቦታዎች ስራ ደግሞ አልተከናወኑም።

ይህን ተከትሎም የአበበ በቂላ ስታዲየም እድሳት ተጨማሪ ስድስት ወራቶችን ያህል እንደሚወስድ ተግልጿል።

ከዚህ በተጨማሪ በ2004 ዓ.ም ተጀምሮ በ2006 ዓ.ም ይጠናቀቃል የተባለውና በአዲስ ዲዛይን እንደገና ማሻሻያ ተደርጎብት በ119 ሚሊዮን ብር ወጪ እየተገባ ያለው በያዝነው ዓመት መጀመሪያ ወራቶች ይጠናቀቃል የተባለው የራስ ኃይሉ መዋኛ ገንዳም ከተያዘለት ጊዜ ተጓቷል።

የራስ ኃይሉ መዋኛ ገንዳ የመጀመሪያ ምዕራፍ ስራው 95 በመቶ እንደጠናቀቀ የተገለጸ ሲሆን ቀሪ የመጀመሪያና የሁለተኛ ምእራፍ ስራዎቹን ለማከናወን ቢያንስ ተጨማሪ ሶስት ወራቶች ያስፈልጋሉ ተብሏል።

የመስክ ጉብኝቱ ከተካሄዳባቸው ቦታዎች መካከል አዲስ እየተገነባ ያለውና 25 ሺህ ተመልካቾችን በወንበር የመያዝ አቅም ያለው የአቃቂ ቃሊቲ ስታዲየም ደግሞ 44 በመቶ ብቻ እንደጠናቀቀ ተገልጿል።

በዛምራ ኮንስራክሽን እየተገነባ ያለው ይህ የአቃቂ ቃሊቲ ስታዲየም በ515 ሚሊዮን ብር ወጪ ነው እየተከናወነ ያለው።

በዛምራ ኮንስታረክሽ የአቃቂ ቃሊቲ ስታዲየም ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር አለምነህ ሽፈራው የአቃቂ ቃሊቲ ስታዲየም አሁን ላይ የኮንክሪት ሙሊት ስራዎች በመጠናቀቅ ላይ ናቸው ብለዋል።

የስታዲየሙ ግንባታ እስከ መጪው ዓመት ህዳር ወር ድረስ ለማጠናቀቅ እየተሰራ እንደሆነ ተገልጿል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ሴቶችና ህጻናት ቋሚ ኮሚቴ ወይዘሮ ፈትሃ መሀመድ ቢሮው እየሰራቸው ካሉ ትላልቅ ማዘውተሪያ ቦታዎች  መካከል የአቃቂ ቃሊት ስታዲየም ግንባታ  ጥሩ የሚባል ደረጃ  እንዳለ ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ የአበበ ቢቂላና ስታዲየም የጥገናና ዙሪያ ሼድ ስራ እና የራስ ኃይሉ መዋኛ ገንዳ ከተቀመጣለቸው ጊዜ የተጓተቱ በመሆኑ ቢሮው ጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል በማድረግ በፍጥነት ሊጠናቀቁ እንደሚገባም አሳስበዋል።