የደብረበርሃን ፖሊቴክኒክ ኮለጅ 20 ሚሊየን ብር ግምት ያለው ሽልማት አገኘ

73

ደብረብርሀን-ሚያዚያ 29/ 2012 ዓም የደብረ ብርሃን ፖሊ ቴክኒክ ኮለጅ በአገር አቀፍ ውድድር 1ኛ በመውጣት 20 ሚሊየን ብር ግምት ያለው ሽልማት ኤፍደብሊዩ ከተባለ ከጀርመን ተራድኦ ድርጅት አገኘ። 

ደብረብርሀን-ሚያዚያ 29/ 2012 ዓ.ም የደብረ ብርሃን ፖሊ ቴክኒክ ኮለጅ በሀገር አቀፍ ውድድር 1ኛ በመውጣት 20 ሚሊየን ብር ግምት ያለው ሽልማት ኤፍ ደብሊዩ ከተባለ ከጀርመን ተራድኦ ድርጅት አገኘ።

የኮለጁ ዲን አቶ ባሻየ በየነ እንደገለጹት ኮሌጁ ለሽልማት የበቃውም በመማር ማስተማርና በምርምር ስራ ውጤታማ ሆኖ በመገኘቱ ነው።

ኮሌጁ ስልጠና በሚሰጥባቸው የቴክኖሎጂና ሌሎች የሙያ ዘርፎች ስራ ፈጣሪና ተወዳዳሪ የሆኑ ሙያተኞችን ማፍራቱን በመረጋገጡ ነው ብለዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ በሃገር አቀፍ ደረጃ በተካሄደው የቴክኖሎጂ ውድድር አንድ የኮሌጁ ሰልጣኝ የፈጠራ ስራውን በማቅረብ ተሸላሚ መሆኑንም አውስተዋል።

በዚህም ኮሌጁ ከአገር አቀፍ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ጋር ተወዳድሮ በማሸነፉ አራት መኪኖችን፣ የማኑፋክቸሪንግና የአውቶሞቲቭ ማሰልጠኛ ማሽኖችንና ኮምፒውተሮችን ለመሸለም በቅቷል።

“ኮሌጁ የጀመረውን ተወዳዳሪነት ለማስቀጠልም የክልሉ መንግስት በመደበው 10 ሚሊየን ብር የበጀት ድጋፍ የማስፋፊያ ግንበታ እያከሄደ ይገኛል”ብለዋል።

በማስፋፊያ ግንባታውም ባለ ሁለት ፎቅ የሆቴልና ቱሪዝም ማስልጠኛና ሁለት የአውቶሞቲቭ ህንጻዎችን ግንባታ እያከሄደ መሆኑን ዲኑ አስታውቀዋል።

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታደሰ ገብረፃዲቅ እንደገለጹት ኮለጁ ስልጠና በሚሰጥባቸው ዘርፎች ብቁና ተወዳዳሪ የሰው ሃይል በማፍራት ለሃገር እድገት የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል።

“በደብረ ብርሃንና አካባቢው በኢንቨስትመንት ለተሰማሩ ባለሃብቶች ቀደም ሲል ያቀርቡት የነበረውን የሰለጠነ የሰው ሃይል ጥያቄ ኮሌጁ በብዛትና በጥራት አሰልጥኖ በማቅረቡ አሁን ላይ መመለስ ተችሏል”ብለዋል።

በተጨማሪም በእንስሳት ማድለብ፣ በወተት ሀብት ልማት፣ በጥቁር አፈር ማጠንፈፍና ሌሎች ችግር ፈቺ የጥናትና ምርምር ስራ የአካባቢውን ምርታማነት እያሳደገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የዞኑ መስተዳድርም ኮሌጁ እያበረከተ የሚገኘውን አስተዋጽኦ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣ አመላክተዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም