ከ2008 እስከ 2011 ዓ.ም የግብር እዳ ያለባቸው ግብር ከፋዮች ወለድና ቅጣት ተነሳላቸው

89

አዲስ አበባ ሚያዝያ 28/2012 (ኢዜአ) የገቢዎች ሚኒስቴር ከ2008 እስከ 2011 ዓ.ም የግብር እዳ ያለባቸውን ግብር ከፋዮች ወለድና ቅጣት ማንሳቱን አስታወቀ።

የገቢዎች ሚኒስትር አቶ ላቀ አያሌው በጉዳዩ ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም በኮሮናቫይረስ ምከንያት ሰራተኞች ከሚሰሩበት ቦታ እንዳይቀነሱ፣ በንግዱ ላይ የሚፈጠረውን ጫና ለመቀነስ ሲባል የእዳ ስረዛው መወሰኑን ገልጸዋል።

በዚህም መሰረት ከ2008 እስከ 2011 ዓ.ም የግብር እዳ ያለባቸው ሰዎች ወለድና ቅጣት የተነሳላቸው መሆኑን አረጋግጠዋል።

በተጠቀሱት ዓመታት የግብር እዳ ያለባቸው ሁሉ የዚህ እድል ተጠቃሚ የሚሆኑት ከዛሬ ጀምሮ በአንድ ወር ውስጥ የፍሬ ግብሩን 25 በመቶ መክፈል ከቻሉ መሆኑንም አስገንዝበዋል።

በአንድ ወር ውስጥ ፍሬ ግብራቸውን 25 በመቶ ክፍያ በመፈጸም ቀሪውን 75 በመቶ ደግሞ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ማጠናቀቅ ይችላሉ ብለዋል ሚኒስትሩ።

እንደ ሚኒስትሩ ገለፃ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ይህን ማድረግ ለቻሉ ሁሉ የ10 በመቶ ከፍሬ ግብራቸው ቅናሽ ይደረግላቸዋል።

ከዚህ በተጨማሪ እስከ ከ2007 ዓ.ም የፍሬ ግብርና የወለድ ቅጣት ያለባቸው ደግሞ ሙሉ በሙሉ እዳው ተነስቶላቸዋል።

የፍሬ ግብር ንብረታቸው የተያዘባቸው ንብረቱ ተመልሶላቸው ወደ ስራ የሚገቡበት ሁኔታ እንደተመቻቸም ተናግረዋል።

ይህ የሚሆነው የተያዘው ተንቀሳቃሽና የማይንቀሳቀስ ሃብት በንግድ ወይም የቢዝነስ እንቅስቃሴ ላይ ከሆነ ነው።

ንብረታቸው ተይዞባቸው የነበሩ ሰዎች፤ ንብረታቸው የሚመለስላቸው ለሶስተኛ ወገን ያልተላለፈና በንግድ ውስጥ እየተንቀሳቀሱ የሚገኙ ከሆነ ብቻ መሆኑንም ተናግረዋል።

በእዳ ምክንያት የተያዘ ቋሚና ተቀሳቃሳቃሽ ንብረት የሚመለሰው ደግሞ ፍሬ ግብሩን መክፍል ሲችሉ እንደሆነ አብራርተዋል።

ተቀሳቃሳቃሽ ንብረት ያላቸውና በአንድ ጊዜ መከፍል ያልቻሉ ፍሬ ግብሩን ከፍለው እስኪጨርሱ የባንክ ዋስትና አቅርበው ንብረታቸውን መወስድና እየሰሩ መክፈል እንደሚችሉም አማራጭ መኖሩን ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

ውሳኔው ከዛሬ ጀምሮ ተግባራዊ ስለሚሆን የግብር እዳ ያለባቸው ሰዎች በገቢዎች ቢሮና ተጠሪ ተቋማት ቅርንጫፍ በመገኘት መገልገል ይችላሉ ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም