ትውልዱ የአንድነት፣ የሰላምና የብልጽግና ፋና ወጊ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ ገለጹ

486

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 27/2012( ኢዜአ) ትውልዱ በቀደምት አርበኞች እግር የተተካ የአንድነት፣ የሰላምና የብልጽግና ፋና ወጊ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓቢይ አህመድ አስታወቁ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ  ዛሬ የተከበረውን 79ኛው የድል በዓል አስመልክተው  በፌስ ቡክ ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት  አዲሱ ትውልድ የቀደምት አባቶቹን አርአያነት በመከተል በጋራ እንዲሰራ አሳስበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያስተላለፉት መልዕክት፦

ከዘመኑ ቀድሞ
ነግቶ የጨለመ፤
ጀግና ወድቋል ከፊት
እኛን እያለመ
ስለኛ እያሰበ።

ከሁሉም ነገር በላይ ሀገርና ሕዝብ አስቀድመው ለነጻነታችን ዋጋ የከፈሉትን አባት እና እናት ዐርበኞች ዛሬ እንዘክራለን።

ስለ ሀገራቸውና ስለ ሕዝባቸው ሲሉ ተዋግተዋል። ለኢትዮጵያ የነበራቸው አቻ የለሽ ፍቅር በደምና በሕይወት መሥዋዕትነት ተገልጧል። ይህንን ያደረጉት እንዲያው ለዝና ሳይሆን በአንድነት ለምትቆም ሉዓላዊት ሀገር ነው።

በቀደምት አርበኞች እግር እንደ መተካታችን፣ እኛ የዚህ ትውልድ አባላትም የአንድነት፣ የሰላም ና የብልጽግና ፋና ወጊዎች ነን። እናቶቻችን እና አባቶቻችን የወሰኑት ታሪካዊ ውሳኔ ነጻነት፣ ሀገርና ሉዓላዊ ሕዝብ ከምንም በላይ መሆናቸውን አሳይቶናል።

ከታሪካችን በመማር ተስፋ መቁረጥን ሳይሆን ዕድገትን፣ ጥላቻን ሳይሆን ፍቅርን፣ኪሣራን ሳይሆን ትርፍን፣ ቀውስን ሳይሆን ብልጽግናን እናያለን።

ክብር ለአርበኞቻችን!