ተመራቂ ተማሪዎች በተመቻቸልን ዕድል እየተደራጀን ነው አሉ

58
አዲስ አበባ ሰኔ 27/2010 የቴክኒክና ሙያ ተመራቂ ተማሪዎች በተመቻቸልን ዕድል በተማርንበት ሙያ እየተደራጀን ነው አሉ። በጄኔራል ዊንጌትና በንፋስ ስልክ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆች የሚማሩ ተማሪዎቹ በተደራጁበት መስክ ስራ ለመጀመር የትምህርት ማስረጃቸውን እየጠበቁ እንደሆነም ነው ለኢዜአ የገለፁት። ተማሪ ፅጌረዳ ግርማና በረከት ወንጌል በጄኔራል ዊንጌት ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የፀጉር ሙያ ተመራቂ ተማሪዎች ሲሆኑ ተደራጅተው ስራ ለመጀመር መነሻ የሚሆን ቁጠባ እንዳስቀመጡ ይናገራሉ። እንደ ተማሪዎቹ ትምህርት ቤቱ እንዲደራጁ ድጋፍ እንዳደረገላቸው ገልጸው በትምህርት ቤቱ ግቢ ውስጥ የሚገኝ አውቶብስን ለስራቸው በሚመች መልኩ በማዘጋጀት እንደተሰጣቸውም ነው የሚናገሩት። ሌሎች ተማሪዎችም በትምህርት ቤቶቻቸው እየተደረገላቸው ስለሚደረገው ድጋፍ ተናግረዋል። ቢላል ሀሊል የጄኔራል ዊንጌት ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የቢዩልዲንግ ኤሌክትሪካል ኢንስታሌሽን ተመራቂ ተማሪ እንዳለው በትምህርት ቤቱ እየተደረገላቸው  ያለው እገዛ በአሁኑ ሰዓት በውጭ ለመደራጀት ሊያስቸግር እንደምችል ገልጾ በቅርቡ ስራእንደምጀምሩ ተስፋ አለው፡፡ ኢዘዲን ቢረዳ የጄኔራል ዊንጌት ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የቢዩልዲንግ ኤሌክትሪካል ኢንስታሌሽን ተመራቂ ተማሪ ትምህርት ቤቱ እንዳደራጃቸው ገልጾ ከዚህ ቦኃላ የትምህርት ማስረጃቸውን ስያስገቡ ስራ እንደምጀምሩ ተናግሯል፡፡ ተማሪዎቹ ሁሉም ተማሪ በስራ ፍለጋ ጊዜውን ከሚያባክን ተደራጅቶ ሊሰራ ይገባል ይላሉ። ፌቨን መንግስቴ የንፋስ ስልክ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የፋሽን ዲዛይን ተመራቂ ተማሪ ተደራጅቶ መስራት ለአሰራሩም ሆነ ለአግባቦቱ ጥቅም እንዳለው ተናግራለች፡፡ ተመራቂዎቹ በራሳቸው ስራ ፈጣሪ እንዲሆኑና ተቀጥረው እንዲሰሩ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የገለፁት ደግሞ የኮሌጆቹ ኃላፊዎች ናቸው። የንፋስ ስልክ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ውጤትን መሰረት ያደረገ ስልጠና ዋና የስራ ሂደት ምክትል ዲን አቶ ዚያዱ ከማል እንደተናገሩት ኮሌጁ ዘንድሮ በመደበኛና በማታው መርሃ ግብር 1 ሺህ 541 ተማሪዎችን ያስመርቃል። ተማሪዎቹ ለመደራጀት የሚረዳቸው ስልጠና እንዳገኙና ከ500 በላይ ተማሪዎች ለመደራጀት ፕሮጀክት መቅረፃቸውን አስረድተዋል። ለ40 ኢንዱስትሪዎችና ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ተማሪዎችን ባላቸው ክፍት ቦታ እንዲቀጥሩ በደብዳቤ ማሳወቃቸውንም ተናግረዋል። በኮሌጃቸው በተያዘው ዓመት የሚመረቁ 1 ሺህ 297 ተማሪዎች እንዳሉ የተናገሩት ደግሞ የጄኔራል ዊንጌት ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዲን አቶ መለሰ ይመር ናቸው። ተማሪዎቹን ከስራ ጋር ለማስተሳሰርም በተሰራው ስራ 52 ተማሪዎች በሰባት ማህበር የተደራጁ ሲሆን ሌሎች በሂደት ላይ እንዳሉም ገልፀዋል። ለ52 ቀጣሪ ድርጅቶች ደብዳቤ መላኩን ገልፀው ሁሉንም ተመራቂ ተማሪዎች በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ከስራ ጋር ለማስተሳሰር እንደሚሰራም ነው የተገሩት። ተማሪዎች ተደራጅተው እንዲሰሩ ወላጅና ባለድርሻ አካላት ሊያግዟቸው ይገባል ያሉት የጄኔራል ዊንጌት ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የምክርና ስራ ማስተሳሰር የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ኃይለማርያም አበበ ናቸው። የአዲስ አበባ ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አንዱአለም ዘውዴ በበኩላቸው ዘንድሮ ከመንግስት የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች የሚመረቁ ከ 8 ሺህ 900 በላይ ተማሪዎች መኖራቸውን ተናግረዋል። ከነዚህም ውስጥ 30 በመቶውን ለማደራጀት ቀሪዎቹን ደግሞ በተለያዩ ቀጣሪ ተቋማት እንዲሰሩ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል። ተመራቂዎችን ከስራ ጋር ለማስተሳሰር ከአራት ሺህ በላይ ተማሪዎች ለመደራጀት የሚያስችል ቁጠባ እንዲጀምሩ መደረጉን ገልፀው ከቀጣሪ ተቋማት ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም