የአደባባይ ስፖርት ተሳታፊዎች በኮሮና ምክንያት መገናኘት ባይችሉም በቤታቸው ሆነው ስፖርቱን አላቋረጡም

76

ባሕርዳር፣ ሚያዚያ 26/2012 (ኢዜአ) በባሕርዳር ከተማ በአደባባይ ስፖርት ሲሳተፉ የነበሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በኮሮና ምክንያት በቤታቸው ውስጥ እንዲሰሩ ማድረጉን የከተማ አስተዳደሩ ባሕልና ስፖርት መምሪያ አስታወቀ።

የመምሪያው ኃላፊ አቶ አብርሃም አሰፋ ለኢዜአ እንደገለጹት በአደባባይ ስፖርት በተለያየ የዕድሜ ደረጃ የሚገኙ ከሁለት ሺህ በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎች በሳምንት ሦስት ቀናት እየተገናኙ እንቅስቃሴ ያደርጉ ነበር።

በማስ ስፖርት የሥራ ዘርፍ የተሰማሩ 15 አሰልጣኞች በመኖራቸው የአደባባይ ስፖርት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየተጠናከረ መምጣቱን ኃላፊው ይናገራሉ።

ይሁን እንጂ አሁን ላይ የተከሰተውን የኮሮና ቫይረስ ሥርጭትን ለመግታት ሲባል የአደባባይ ስፖርት እንዲቆም ተደርጎ ስፖርተኞቹ በቤታቸው ውስጥ የተለመደውን እንቅስቃሴ እንዲሰሩ ተደርጓል።

እንዴት መሥራት እንዳለባቸውም በስልክ፣ በቴሌቪዥን፣ በራዲዮና በማኅበራዊ ሚዲያ እየተላለፈ መሆኑን ጠቁመው ዘላቂ ችግራቸውን የሚፈታ የማስ ስፖርት ማኅበር በመመሥረት ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

የማስ ስፖርት አሰልጣኝ የሆነው ወጣት ይልቃል ባየ እንዳለው በዘርፉ ላለፉት 11 ዓመታት በትምህርት ቤት የማስተማርና ብዙሃኑን የማሠልጠን ልምድ አለው።

ከ350 በላይ ስፖርተኞችን በጂም ቤቱና በአደባባይ ላይ ስፖርት እያሰለጠነ እንደነበር ገልጾ አሁን ላይ ከኮሮና ቫይረስ መምጣት ጋር ተያይዞ ሁሉም ሠልጣኞች በቤታቸው ሆነው እንዲሰሩ ተደርጓል።

በቤት ውሰጥ የሚሰራው የስፖርት ዓይነት የልብ ምትን የሚያስተካክል፣ የደም ዝውውርን የሚያፋጥንና የአተነፋፈስ ሥርዓት የሚያስተካከል እንቅስቃሴ መሆን እንደሚገባው መክሯል።

በማስ ስፖርት የሚሳተፉት ወይዘሮ ሰላማዊት ብርሃኑ እንዳሉት “አሁን ላይ በኮሮና ምክንያት ከቤት ብቀመጥም ስፖርታዊ እንቅስቃሴ አላቋረጥኩም” ብለዋል።

በተለይም ጧት ጧት በቴሌቪዥን የሚተላለፉ ስፖርታዊ ፕሮግራሞች በአሠልጣኛቸው በተነገራቸው የስፖርት እንቅስቃሴ መሠረት ሣይንሳዊ መንገዱን ጠብቀው እንዲሰሩ እንዳገዛቸው ገልጸዋል።

የአደባባይ ስፖርት ጤንነትን ከመጠበቅ፣ አካላዊ፣ አእምሯዊና ሥነልቦናዊ ጥንካሬ እንዲኖር ከማድረግ ባሻገር ለማኅበራዊ ትሥሥር ፋይዳው የጎላ በመሆኑ ኮሮና ጠፍቶ ከጓደኞቻቸው ጋር የሚገናኙበትን ጊዜ መናፈቃቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም