በደቡብ ክልል ተፈናቃዮችን መልሶ ለማቋቋም እየተሰራ ነው

52
ሃዋሳ ሰኔ 27/2010 በደቡብ ክልል በጸጥታ ችግር ምክንያት ከተለያዩ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ሰዎችን መልሶ ለማቋቋም የሚያስችሉ ሥራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን የክልሉ የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡ የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ሰለሞን ኃይሉ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳሉት ከኦሮሚያ ክልል ምዕራብና ምስራቅ ጉጂ ዞን የተፈናቀሉ የጌዴኦ ብሔር ተወላጆችን ጨምሮ በሲዳማ፣ ካፋና ሰገን አካባቢ ዞኖች የተፈናቀሉትን ካሉበት አስቸጋሪ ሁኔታ ለማውጣት እየተሰራ ነው፡፡ ከምዕራብና ምስራቅ ጉጂ ዞን በርካታ ቁጥር ያላቸው የጌዴኦ ብሔር ተወላጆች የተፈናቀሉ ሲሆን በተመሳሳይ ከምዕራብ ጉጂ ዞን በሺዎች የሚቆጠሩ የኮሬ ብሔር ተወላጆች መፈናቀላቸውን ጠቁመዋል፡፡ በሲዳማና ካፋ ዞን በተፈጠረ ሁከትም ተጨማሪ ሰዎች መፈናቀላቸውንና አጠቃላይ በግጭት የተፈናቀሉትን ወገኖች መልሶ ለማቋቋምም ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለማሰባሰብ የተለያዩ የገቢ ማስገኛ ሥራዎች እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡ በገቢ ማስገኛ ሥራው መላው ሕብረተሰብ እንደሚሳተፍና የመልሶ ማቋቋም ሥራ ዕቅድ ተዘጋጅቶ ተግባራዊ የማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡ "ተከስቶ በነበረው ችግር ምክንያት በርካታ ንብረት ወደሟል፤ የሰው ሕይወትም ጠፍቷል፤" ያሉት አቶ ሰለሞን ከመልሶ ማቋቋም ስራው በተጨማሪ በህዝቦች መካከል አንድነትን የሚያጠናክሩ ስራዎች እንደሚሰሩ ገልጸዋል። እስካሁን ባለው ሂደት ለተፈናቀሉ ወገኖች የዕለት ደራሽ እህል አቅርቦት ሥራ እየተከናወነ መሆኑንና ለመልሶ ማቋቋም ተግባሩ ሰባት ዋና ዋና ሥራዎች መለየታቸውን አስታውቀዋል፡፡ ከተለዩት ስራዎች መካከል የተፈናቃዮችን የወደመ ንብረትና የጉዳት መጠን መረጃ ለይቶ የማሰባሰብና የማደራጀት እንዲሁም ገቢ አሰባሳቢ ኮሚቴ የማዋቀር ሥራ ይጠቀሳሉ። በተጨማሪም በህዝቦች መካከል ያለውን የመጠራጠር ስሜት ለመቅረፍ የሚያስችል ህዝባዊ የውይይት መድረክ ለማዘጋጀትና ድጋፍ ለሚያደርጉ አካላት የባንክ አካውንት የመክፈት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን አስረድተዋል። አቶ ሰለሞን እንዳሉት በጸጥታ ችግሩ ምክንያት ረዳትና ጧሪ ያጡ እንዲሁም የትዳር አጋሮቻቸውና ጧሪ ልጆቻቸው የሞቱባቸው ራሳቸውን በዘላቂነት እንዲችሉ የሥራ ዕድል የመፍጠር ሥራ ይሰራል፡፡ በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ዜጎችን በዘላቂነት ለማቋቋም መላው ሕብረተሰቡ፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ ያቀረቡት አቶ ሰለሞን ከገንዘብ በተጨማሪ የተለያዩ አልባሳትና ቁሳቁስ መለገስ እንደሚቻልም ገልጸዋል፡፡ በገንዘብ ድጋፍ ማድረግ የሚፈልጉ አካላት ለዚህ ተግባር ተብሎ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተከፈተው የባንክ ሒሳብ ቁጥር 1000251170898 ማስገባት እንደሚችልም አስታውቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም