የግንባታ ሂደቱ የተጓተተው የሳንሱሲ-ታጠቅ-ኬላ መንገድ አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ተባለ

85

አዲስ አበባ፣ሚያዚያ 24/2012 (ኢዜአ) የግንባታ ሂደቱ የተጓተተው የሳንሱሲ-ታጠቅ-ኬላ የ13 ነጥብ 5 ሚሎ ሜትር የኮንከሪት አስፋልት መንገድ አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ተገለጸ።

የኢትዮጵያ መንግዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሃብታሙ ተገኝ፣ ተቋራጭ ድርጀቱ፣ ሌሎች ከፍትኛ የስራ ሃላፊዎችና የቡራዩ ከተማ አስተዳደር የስራ ሃላፊዎች የመንገዱን የግንባታ ሂደት ጎብኝተዋል።

በቡራዩ ከተማ አስተዳደር የገፈርሳ አካባቢ ነዋሪ አቶ አለሙ ጫላ ለኢዜአ እንደገለጹት የመንገዱ ግንባታ መዘግየት በአካባቢው እንቅስቃሴ ላይ ችግር ፈጥሯል።

የመንገዱ ግንባታ ከተጀመረበት ከህዳር 2010 ዓ.ም ጀምሮ ላለፉት ሁለት ዓመታት በነዋሪዎች ዕለታዊ እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ጫና ማሳደሩንም ተናግረዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በጥሩ ሁኔታ ግንባታው እየተካሄደ  መሆኑን የታዘቡት አቶ አለሙ የአካባቢው ነዋሪም የመንገዱን መጠናቀቅ በተስፋ እየተጠባበቀ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሃብታሙ ተገኝ ከጉብኝቱ በኋላ እንደተናገሩት በአሁኑ ወቅት የፕሮጀክቱ አፈጻጸም መገባደድ ነበረበት።

ባለስልጣኑ ለሚያከናውናቸው የመንገድ ፕሮጀክቶች የወሰን ማስከበር ችግር ትልቁ ማነቆ ሆኖ ቀጥሏል ያሉት ኢንጂነር ሃብታሙ፤ የወሰን ማሰከበር ክፍያውም ከጊዜ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ ባለፈው በጀት ዓመት ለባለሥልጣኑ ከተመደበው 28 ቢሊዮን ብር 4 ቢሊየኑን ለዚሁ ወጭ ማድረጉን ጠቅሰዋል።

በሳንሱሲ-ታጠቅ-ኬላ መንገድ ፕሮጀክትም በርካታ ነዋሪዎች ካሳ ሳይከፈላቸው ቀድመው በማፍረስ ትብብር ቢያደርጉም፣ የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ክፍያ ቢፈጸምላቸውም በተፈለገው ፍጥነት ሃላፊነታቸውን አለመወጣታቸውን ተናግረዋል።

በዚህም አሁን ላይ ፕሮጀክቱ ከአንድ ወር በኋላ መጠናቀቅ ቢኖርበትም አፈጻጸሙ 40 በመቶ ብቻ ነው።

ለመንገዱ ግንባታ መጠናቀቅ የሁሉንም ተቋማት ቅንጅታዊ ስራ ስለሚጠይቅ ተቋማቱ ሃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።

ፕሮጀክቱ በወሰን ማስከበር ችግር ለረጅም ጊዜ ሳይሰራ መቆየቱን የገለጹት ኢንጅነር ሃብታሙ የመንገዱ ግንባታ የወሰን ማስከበር ስራዎች ተጠናቀው አመት ባልሞላ ጊዜ ይጠናቀቃል ብለዋል።

ቤታቸው ለፈረሰባቸው ዜጎች ቀሪ ያልተከፈለ የካሳ ክፍያም በቀጣይ ሳምንት ጀምሮ እንደሚከፈል ገልጸው፤ ሌሎች የአገልግሎት ተቋማቱ ስራቸውን ካከናወኑ በወራት ውስጥ ስራው ሊጠናቀቅ እንደሚችል ተናግረዋል።

የቡራዩ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ሃይሉ ደራርሳ እንዳሉትም ህብረተሰቡ የመንገዱን መገንባት በመደፈለግ ካሳ ሳይቀበል መኖሪያ ቤቱን በማፍረስ ከአመራሩ በተሻለ ትብብር ቢያድርግም ፕሮጀክቱ ግን በታቀደለት ጊዜ እንዳልተራመደ ይናገራሉ።

ከተማ አስተዳደሩ መንገዱ በፍጥነት ተገንብቶ ለአገልግሎት እንዲበቃ የሚጠበቅበትን ሃላፊነት ለመወጣትም ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋለ።

የመንገዱ ግንባታ ተቋራጩ የአሰር ኮንስትራከሽን ስራ አስኪያጅ አቶ ኤፍሬም ቢያድግልኝ፤ ቀሪ የወሰን ማስከበር ተግባራት በፍጥነት ከተጠናቀቁ መንገዱን ዓመት ባልሞላ ጊዜ ማጠናቀቅ ይቻላል ብለዋል።

እስከሁንም የወሰን ማስከበር ስራዎች የተከናወነባቸው የመንገድ ፕሮጀክቱ ከፍሎች ረጅም ጊዜ የሚጠይቁ ቢሆንም በወራት ውስጥ በፍጥነት ማከናወን መቻሉን ገልጸዋል።  

አሁን ላይ  16 ሜትር ርዝመት ያለውን የገፈርሳ ወንዝ ድልድይን ጨምሮ ሌሎች የድልድይ ስራዎች፣ የውሃ ማፋሰሻ ቱቦ ቀበራ፣ ከወሰን ማስከበር ነጻ የሆኑ የአንድ አቅጣጫ አስፋልት ንጣፍ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

ክረምቱ ከመግባቱ በፊት አፈጻጸሙን 50 በመቶ በማሳደግ በቀጣይ ከመስከርም ወር ጀምሮ ደግሞ ቀሪውን 50 በመቶ አጠናቆ ለአገልግሎት ለማብቃት መታቀዱን ገልጸዋል።

13 ነጥብ 5 ኪሎሜትር የሚረዝመው የሳንሱሲ-ታጠቅ-ኬላ መንገድ ግንባታው ሲጠናቀቅ በግራና በቀኝ በአንድ ጊዜ 4 ተሽከርካሪዎችን የማስተናገድ አቅም አለው።

ከአዲስ አበባ ወደ ምዕራብ ኢትዮጵያ ለሚደረጉ የወጭና ገቢ ንግድ አማራጭ መውጫ ጎዳናነቱ ባሻገር ለአካባቢው ኢንዱስትሪ ተሽከርካሪዎችም መጨናነቅን በመቀነስ ረገድ የጎላ ሚና ይኖረዋል ተብሏል።

ፕሮጀክቱ በ820 ሚሊየን ብር ወጭ በአስፓልት ኮንክሪት ደረጃ የሚገነባ ሲሆን ወጭውም ሙሉ ለሙሉ በኢትዮጵያ መንግስት የሚሸፈን ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም