ስለ ሠራተኛው ማኅበረሰብ ስንነጋገር ስለ ቀጣይዋ ኢትዮጵያ እየተነጋገርን እንደሆነ እናምናለን -ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ

85

አዲስ አበባ ሚያዝያ 23/2012 (ኢዜአ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለዓለም የሠራተኞች ቀን የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ስተላልፈዋል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ ሚያዝያ 23 ቀን (ሜይ አንድ) የሚከበረው የዓለም የሠራተኞች ቀን የዓለም ሠራተኞችን ሕይወት የቀየሩ የሠራተኞች ትግሎች የሚታወሱበት ቀን ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው ።

ሠራተኛው የኀብረተሰብ ክፍል ለሚሰጠው አገልግሎት ተመጣጣኝ ዋጋ እንዲከፈለው፣ ለተመሳሳይ ሥራ ተመሳሳይ ክፍያ እንዲኖር፣ በሥራ አካባቢው የሥራ ዋስትናና ደኅንነቱ እንዲጠበቅ፣ ሰብአዊ መብቱ እንዲረጋገጥ፣ የመደራጀት መብቱ እንዲከበር፣ የተደረጉ አያሌ ትግሎች አሉ ነው ያሉት።

በሀገራችን ምንም እንኳን የሠራተኛው ቁጥር አነስተኛ ቢሆንም ለመብትና ለነጻነቱ ያደረገውና ዛሬም የሚያደርገው ትግል ግን ከቁጥሩ በላይ ታሪክ የቀየረ መሆኑን አንስተዋል፡፡

አሁን ያለንበት ዘመን በዓለም አቀፍ ደረጃም ሆነ በሀገር ውስጥ እንደ ጥንቱ ዘመን፣ ‹ዓለም የወዛደሮች ትሆናለች› ተብሎ ብቻ የሚፎከርበት እንዳልሆነ የገለጹት ዶ/ር ዐቢይ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ዓለም ከሠራተኛ ልጆቿ ውጭ ምንም ናት ብለዋል፡፡

የሀገራችንም ጉዞ አምራች ኢንዱስትሪውን ወደ ማስፋፋት የሚደረግ በመሆኑ ስለ ሠራተኛው ማኅበረሰብ ስንነጋገር ስለ ቀጣይዋ ኢትዮጵያ እየተነጋገርን እንደሆነ እናምናለን ነው ያሉት፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳብራሩት ስለ ሠራተኛው የኑሮ፣ የሥራና የጤና ሁኔታ ስናስብ፣ የሠራተኛውን መብቶችና ጥቅሞች ስናስብ፣ የሠራተኛውን የሥራ ዋስትናና ዕድገት ስናስብ፤ ስለ ነገዋ ኢትዮጵያ እያሰብን ነው፡፡

በመሆኑም በሠራተኛው እና በአሠሪው መካከል የሚኖረው ግንኙነት የነገዋን ኢትዮጵያ ታሳቢ ያደረገ ግንኙነት እንዲሆን ተስፋ ይደረጋል፡፡

ትብብር እና መደጋገፍን መሠረት ያደረገ፣ በሕግና በሞራል የሚመራ፣ የሠራተኛውን መብት ከሀገሪቱ ዕድገትና ከኢንዱስትሪው ሰላም ጋር ያጣጣመ መሆን ይኖርበታል በማለት ነው የተናገሩት፡፡

የሠራተኞች መብት የማይከበርበት ኢንዱስትሪ ሕይወት አልባ ኢንዱስትሪ ነው፡፡

ኢንዱስትሪያቸው ሰላምና ትርፋማ እንዲሆን የማይሠሩ ሠራተኞችም ራሳቸውን በራሳቸው የሚያጠፉ ሠራተኞች ናቸው ብለዋል፡፡

"ሠራተኞችና አሠሪዎች ለአንድ ሀገራዊ ግብ የሚሠሩ ሁለት አካላት ናቸው፡፡ ተደጋግፈውና ተግባብተው፣ተደራድረውና ተስማምተው እንጂ ተቃርነውና ተጋጭተው ውጤታማ አይሆኑም፡፡ ተባባሪነት እንጂ ባላንጣነት አያዋጣቸውም" ሰሊሉ ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በጥናትና በድፍረት ወደ ኢንዱስትሪው የሚገቡ፣ ችግሮችን ተቋቁመው የሚያልፉ፣ ትውልድ ተሻጋሪ ማምረቻዎችን የሚተክሉ ባለ ሀብቶችን እንፈልጋለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የባለሃብቶቹን ራእይ ወደ ተግባር የሚለውጡ፣ በሙያና በዲሲፕሊን የታነጹ ሠራተኞችንም እንፈልጋለን፡፡ ይህም የነገው ብልጽግናችን የሁለቱ ድምር ውጤት ነው ብለዋል፡፡

አሠሪዎች የሠራተኞችን መብት ማክበር ያለባቸው፣ ጥቅሞቻቸውን መጠበቅ ያለባቸው፣ መደራጀታቸውን መደገፍ ያለባቸው ለራሳቸው ሲሉ ጭምር ነው በማለትም ጠቅሰዋል።

ክብሩና ጥቅሙ ያልተከበረለት ሠራተኛ ምርታማ፣ ውጤታማና ጤናማ አይሆንም፡፡ ሠራተኞችም የኢንዱስትሪውን ትርፋማነት፣ደኅንነት፣ ወጭ ቆጣቢነት፣ ሰላምና ዘላቂነት ማስጠበቅ ያለባቸው የመኖራቸው ምክንያት፣ የሀገራቸውም የዕድገቷ መሠረት ስለሆነ ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፡፡

የዘንድሮው የዓለም የሠራተኞች ቀንም በዚህ መንፈስ ሊከበር እንደሚገባው ገልጸው፤ የዘንድሮው የሠራተኞች ቀን የሚከበረው በኮሮና ወረርሽኝ ውስጥ በሆነች ዓለም ነው፡፡

ወረርሽኙ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የጤና፣ የማኅበራዊ ደኅንነት፣ ወዘተ. ፈተና ሆኖ መጥቷል ብለዋል፡፡

ወረርሽኙ ለሠራተኞች ከባድ የሆነ የሥራ ዋስትና ሥጋት በመፍጠሩና በተለይም በሀገራችን በእግሩ መሄድ የጀመረውን የማምረቻ ኢንዱስትሪ ወደ ዳዴ እንዳይመልሰው ማድረግ ይገባናል ሲሉም ተናግረዋል፡፡

በከፍተኛ ጥበብ፣ ኃላፊነትና ቁርጠኝነት መሥራት ያለብን ጊዜ ነው፤መንግሥት በአንድ በኩል የሠራተኞች የሥራ ዋስትና እንዲጠበቅ፣ በሌላ በኩል ደግሞ አምራች ኢንዱስትሪው በወረርሽ ተጽዕኖ ሳይሰበር እንዲቀጥል ለማድረግ አስፈላጊ ርምጃዎችን እየወሰደ ነው በማለት ገልጸዋል፡፡

ከተለያዩ አካላት ጋር በመሆንም አስፈላጊውን ድጋፍ እየሰጠ ይገኛል ያሉ ሲሆን ሠራተኛው በአንድ ጎን የገጠመንን ፈተና ሊያካክስ በሚችል መልኩ የበለጠ መሥራት ይጠበቅበታል በማለት አስገንዝበዋል፡፡

በሌላ ጎን ደግሞ ሰራተኛው ራሱን፣ ቤተሰቡንና ሌሎችን ከበሽታው በመጠበቅ የበሽታውን ተጽዕኖና እድሜ ለመቀነስ መጣር ይኖርበታል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥራችንን በቤታችን ወይም ተገቢውን ጥንቃቄ አድርገን በሥራ ቦታችን ማከናወን አለብን እንጂ ለአፍታም መታከት አይገባንም ብለዋል፡፡

ወቅቱን የማረፊያ ሳይሆን አብዝቶ የመሥሪያና፣ ብዙ የማትረፊያ አድርጎ መውሰድ ይገባል፡፡ ወቅቱ ብክነትን በመከላከልና ወጭን በመቆጠብ የምንሠራበት ወቅት ነው በማለትም ገልጸዋል።

አዳዲስ ፈጠራዎችን ተጠቅሞ ለገጠመን ፈተና መፍትሔ በማፈላለግ፣ ከፍተኛ ወጭ የምናወጣባቸውን የውጭ ምርቶች በሀገር ውስጥ በመተካት፣ ያለንን ዕውቀትና ሀብት ከሌሎች ጋር በመካፈል፣ ይሄንን ወቅት ተጋፍጠን ልናሸንፈው ይገባል በማለት አጽንዖት ሰጥተው ተናግረዋል ፡

ከፊታችን የተቀመጠው አማራጭ ሁለት ነው በማለት የገለጹት ዶ/ር ዐቢይ ወይ ኮሮና በእኛ ላይ ያልፋል፤ አለያም እኛ በኮሮና ላይ እናልፋለን ብለዋል፡፡

ኮሮና ሲያልፍ ኮሮና ካመጣብን ችግር ይልቅ ችግሩን ለመቋቋም ስንል በፈጠርናቸው መፍትሔዎች፣ ባፈለቅናቸው ሐሳቦች፣ በከፍተኛ ሁኔታ ባመረትናቸው ምርቶች፣ በየአካባቢያችን በፈጠርናቸው ትብብሮች፣ ከጊዜ፣ ከዕውቀትና ከገንዘብ በከፈልናቸው መሥዋዕትነቶች የምናስታውሰው ከሆነ፤ እኛ በኮሮና ላይ ድል አድርገን አልፈናል ማለት ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ኮሮና ሲያልፍ አብሮን የሚቀረው ያጋጠመን ኪሣራ፣ ያለቀብን ወገን፣ የፈጠርነው ዝርክርክነት፣ ያልሠራነው ሥራ፣ ያልወሰንነው ውሳኔ፣ ያልከፈልነው መሥዋዕትነት ከሆነ፣ ኮሮና በእኛ ላይ አድቅቆን አልፏል ማለት ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው፡፡

የኢትዮጵያ ሠራተኞች እኛ በኮሮና ላይ እንድናልፍ እንጂ፣ ኮሮና በእኛ ላይ እንዲያልፍ እንደማይፈቅዱ እምነቴ የጸና ነው በማለት፤ ለዚህም ከነገው ጊዜ ተበድራችሁ ዛሬ የምትችሉትን ሁሉ እንድታደርጉ ጥሪ አቀርባለሁ በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም