የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አገልግሎት አሰጣጡን የሚያቀላጥፍ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተግባራዊ አደረገ

76

አዲስ አበባ ፣ሚያዚያ 22/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለደንበኞቹ ዘመናዊ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችለውን ቴክኖሎጂ ተግባራዊ ማድረጉን አስታወቀ፡፡

የባንኩ ፕሬዚዳንትና ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አቤ ሳኖ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ላይ እንደጠቀሱት፤ ባንኩ በዘመናዊ መልክ ተግባራዊ ያደረገው ቴክኖሎጂ ከስምንት ዓመት በፊት ወደ ስራ ያስገባውን የኮር ባንኪንግ አገልግሎት የሚያሻሽል ነው፡፡

ቴክኖሎጂው ኅብረተሰቡ ቀልጣፋና ዘመናዊ  አገልግሎት እንዲያገኝ  የሚያስችል  እንደሆነም ጠቁመዋል።

የኮር ባንኪንግ አገልግሎት ከ8 ዓመት በፊት ሲጀመር 201 ቅርንጫፎችን በማስተሳሰር እንደነበር ያወሱት አቶ አቤ፤ ተግባራዊ የተደረገው ቴክኖሎጂ 1 ሺህ 587 ቅርንጫፎችንና 107 ንዑሥ ቅርንጫፎችን እንዲሁም የዋናው መስሪያ ቤት የስራ ክፍሎችን የሚያስተሳስር መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ይህን ዘመናዊ አሰራር ለመዘርጋት ባንኩ ካሉት በርካታ ደንበኞች አንፃር  የተለያዩ  ተግዳሮቶች ገጥመውት እንደነበር ገልጸዋል።

አዲስ የተሻሻለው የኮር ባንኪንግ አገልግሎት ለህብረተሰቡ ቀላል፣ ምቹ፣ ቀልጣፋና  ተመራጭ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል መሆኑን አቶ አቤ አብራርተዋል፡፡

ከስምንት አመት በፊት የኮር ባንኪንግ አገልግሎት ሲጀመር ባንኩ የነበሩት የደንበኞቹ ቁጥር ከሶስት ሚሊዮን ያልበለጠ እንደነበር  አስታውሰው፤ ዛሬ ላይ የደንበኞች ቁጥር 25 ሚሊዮን መድረሱንም አስገንዝበዋል፡፡

አዲሱን  ሲስተም ለማዋቀር ባንኩ ለአንድ ሳምንት ያህል መዘጋት ቢኖርበትም  በባንኩ  ሰራተኞች ጥረት ስራው በሁለት ቀን ከግማሽ በተሳካ ሁኔታ ሊጠናቀቅ  መቻሉንም  አስገንዝበዋል፡፡

''አገልግሎቱን ለማሳደግ በተደረገው ጥረት በቀጣይ የሲስተም መቋረጥም  ሆነ  የአሰራር  መጓተት አይኖርም'' ብለዋል፡፡

ቴክኖሎጂው ወደፊት ለደንበኞች ምቹ፣ ቀልጣፋና የላቀ አገልግሎት ለመስጠት  የሚያስችለው እንደሚሆንም አቶ አቤ ሳኖ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም