ኢትዮጵያ ዓረቡ ዓለም የሚያራምደውን የተሳሳተ ትርክት ለማረም በሚዲያና ዲፕሎማሲ ዘርፉ መስራት አለባት

73

አዲስ አበባ፣ሚያዚያ 22/2012 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ ዓረቡ ዓለም የሚያራምደውን የተሳሳተ ትርክት ለማረም በሚዲያና ዲፕሎማሲ ዘርፉ ላይ ልትሰራ ይገባል ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የኢትዮ-ዓረብ ተማራማሪና ተንታኞች ተናገሩ።

በዓለማችን ረጅሙ ወንዝ ሰማያዊ ናይል ወይንም ዓባይ ጉዳይ ግብፅ ዘመን የማይሽረው የ'እኔ ብቻ' አመለካክት አንግባ በኢትዮጵያ ላይ ከዛቻ እስከ ዘመቻ የደረሰ ታሪካዊ የባላንጣነት እይታ ይዛ ቀጥላለች።

'ግብጽ የዓባይ ስጦታ ናት' በሚል ብሂል የምትመራው ግብጽ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በፊት ጀምሮ ከዓለማችን ግዙፍ የውሃ ግድቦች የሚመደቡ ፕሮጀክቶችን ገንብታ የዜጎቿን ሕይወት ለውጣለች፤ እንደ አገርም ሁለንተናዊ አቅሟን አጎልብታለች።

በአንጻሩ ከ86 በመቶ በላይ የዓባይን ወንዝ ፍሰት የምትሸፍነውና ለም አፈሯንም በየዓመቱ የምትለግሰው የዓባይ ወንዝ መነሻዋ ኢትዮጵያ ግን ወንዙ ተገድቦ ልትጠቀም ይቅርና በየክረምቱ በውሃ ሙላት የዜጎቿን ሕይወት ከመነጠቅ ማዳን አልቻለችም።

ከዚህ ባለፈ ኢትዮጵያ በወንዞቿ ግብርናዋን ማዘመን ቀርቶ በአሁኑ ወቅት እንደቅንጦት የማይታየውን የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽ በማድረግ ጨለማውን መግፈፍ፤ ዜጎቿን ከኩራዝ ጭላንጭል ማላቀቅም ተስኗታል።

ኢትዮጵያ በድርቅ፣ ርሃብና ድህነት የመንገላታቷ አንዱ ምስጢር የተፈጥሮ ሃብቷን በአግባቡ  አልምታ ያለመጠቀሟ ጉዳይ ቢሆንም ቅሉ ኢትዮጵያ እንዳትለማና እንዳትበለጽግ ግብጽ በየዘመናቱ ጫናዋን ከማሳረፍ አልተቆጠበችም።

ከብዙ ጥረት በኋላም ቢሆን ከዘጠኝ ዓመታት በፊት ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ በጀመረችው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ግብጽ የነበራትን ታሪካዊ ጫና በመቀጠል ግድቡን የማስተጓጎል ጥረት፣ ዛቻና ማስፈራራቷን ቀጥላለች።

ዓለም አቀፍ ተቋማትና የዓረብ ዓለም አገራትን ጨምሮ በዲፕሎማሲያዊ አቅሟ ከጎኗ በማሰለፍ በኢትዮጵያ ላይ ስታደርግ የነበረውን ተጽዕኖ ለማሳደር እየኳተነችም ትገኛለች።

በጉዳዩ ላይ ለኢዜአ ሃሳባቸውን ያጋሩ በኢትዮጵያና በመካከለኛው ምስራቅ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ተንታኝና ተመራማሪዎች ግብፅም ሆነ ሌሎች የመካከለኛው ምስራቅ አገራት ኢትዮጵያን የሳሉበትን የተሳሳተ ትርክት ያምናሉ።

ለዚህም መነሻው መሬት ላይ ያለውን እውነታ እንዲረዱ ለማሳመን በኢትዮጵያ በኩል ክፍተት በመኖሩ እንደሆነ ይገልጻሉ።

በዓባይ ጉዳዮች ተንታኝና ጋዜጠኛው አቶ አንዋር ኢብራሂም በግብጽ ሚዲያዎች በኩል የሚነዛውና በኢትዮጵያ ያለው ዕውንታ የማይገናኝ እንዲሁም ኢትዮጵያ በአረቡ ዓለም የምትሳልበት መንገድ የተዛባ እንደሆነ ይናገራል።

'ዓባይ የፖለቲካ አጀንዳ መሆን አልነበረበትም' የሚለው ጋዜጠኛው፣ የአረብ አገራት ኢትዮጵያን የሚመለከቱበት መንገድ ከእስራኤል ጋር የተያያዘና የተሳሰተ አካሄድ መሆኑን ይገልጻል።

ኢትዮጵያ ለአገርና ለህዝብ ልማት ሳይሆን ሌሎችን ለመጉዳት እንደምትሰራ ግብጽ ሰፊ ቅስቀሳ በማድረግ ሌሎች ከጎኗ እንዲሰለፉ አጠንክራ እየሰራች መሆኑንም ነው ያብራረው።

ሌላው የአፍሪካ አረብ ጉዳዮች ተመራማሪ አቶ ኑረዲን አብዳ በበኩላቸው በዓባይ ጉዳይ በኢትዮጵያ ያለውን ዕውነታ እንዲሁም የግብጽ ሚዲያዎችን የተሳሳተ አቋም ለማስረዳት ሌሎች አገራት እንደሚያደርጉት አማካሪዎችንና ተንታኞችን መጠቀም ተገቢ ነው ባይ ናቸው።

ለዚህም በሚዲያ የተደራጀ ስትራቴጂ መንደፍና ኢንቨስት አድርጎ መስራት እንደሚገባ አስረድቷል።

በአረብ ሊግ አገራት የተከበበችው ኢትዮጵያ ለመካከለኟው ምስራቅ አገራት እውነታውን በዝርዝር ተደራሽ ለማድረግ እንደ አረብኛ አይነት ቋንቋዎችን ተጠቅማ መስራት እንዳለበት ነው የተናገሩት።

በሌላ በኩል አገራቱ በኢትዮጵያ ላይ ስላላቸው የተዛባ ምስል የሚተነትንና የሚያስረዳ የሚዲያ ኤክስፐርት ሊኖራት ይገባል ሲሉ ተንታኞቹ ይናገራሉ።

የኢትዮጵያ ሚዲያዎችም ለኢትዮጵያዊያን ሳይሆን ለውጭ ዓለም የሚሆኑ ሥራዎች ላይ እንዲሰሩ መንግስትም ለዚህ ድጋፍ ማድረግ እንዳለበት አንስተዋል።

በኢትዮጵያና በመካከለኛው ምስራቅ ግንኙነት ላይ ተመራማሪው አብዲሽኩር አብዱሰመድ በጥናት ከተደገፉ የሚዲያና ኮሚኒኬሽን ሥራዎች ባሻገር የመንግስትና የፐብሊክ ዲፕሎማሲም ላይ ማተኮር ይገባል፤ የዓረቡ ዓለምን ለማሳመንም ጊዜው አሁን ነው በማለት ይጠይቃሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም