ምክር ቤቱ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ያጋጠመውን አደጋ ለመቀነስ የኢኮኖሚ ማነቃቂያ እንዲተገበር ወሰነ

781

አዲስ አበባ ሚያዚያ 20/2012 (ኢዜአ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ያጋጠመውን አደጋ ለመቀነስ የተዘጋጀ የኢኮኖሚ ማነቃቂያ ሥራ ላይ እንዲውል ወሰነ።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት በኮሮና ቫይረስ ምክንያት በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ያጋጠመውን አደጋ ለመቀነስ መወሰድ ስላለባቸው እርምጃዎች ላይ በቀረበ የውሳኔ ሀሳብ ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ።

ምክር ቤቱ ሰሞኑን ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባው በቫይረሱ ምክንያት በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ያጋጠመው አደጋ የአብዛኛውን ኅብረተሰብ ክፍል ኑሮ እንደሚጎዳ ተመልክቷል።

ከዚህ በመነሳትም መንግሥት ዘርፈ ብዙ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን አስታውሶ፣የድጋፍ  አካል የሆነውን የኢኮኖሚ ማነቃቂያ ማድረግ እንዳስፈለገ ገልጿል።

ወረርሽኙ በኅብረተሰቡ ጤና ላይ የሚደርሰውን አደጋ ለመከላከል የሚወሰዱ እርምጃዎች ውጤታማ እንዲሆኑ፣ ሠራተኞች ከሥራ እንዳይሰናበቱና የድጋፍ እርምጃ እንዲወስዱ ለማድረግ የገንዘብ ሚኒስቴር ለምክር ቤቱ ባቀረበው የውሳኔ ሀሳብ ላይ ከተወያየ በኋላ አንዳንድ ማስተካከያዎችን በማከል ሥራ ላይ እንዲውል ወስኗል።

በተጨማሪም የኮሮና ቫይረስ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመከላከል መንግሥት ለሚያደርገው ጥረት የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርጉ ዜጎች እንዲበረታቱ በጎ አድራጊዎች ለመንግሥት የሚያደርጉት የገንዘብ ድጋፍ ግብር ከሚከፈልበት የ2012 ግብር ክፍያ ላይ የ20 በመቶ ያልበለጠ ተቀናሽ ይደረጋል።

እንዲሁም የተጨማሪ እሴት ታከስና ተርንኦቨር ታክስ የሚያስታውቁበትና የሚከፍሉበት ጊዜ በአንድ ወር እንዲራዘም ማድረግን፣ የንግድ ድርጅቶች በሥራ ላይ በቆዩባቸው ጊዜያት ያጋጠማቸው ኪሳራ ማሸጋገርን፣ በስራ መቀዛቀዝ ምክንያት የጡረታ መዋጮን ለመክፈል የተቸገሩ አሰሪዎች የሚቀጥሉትን ሶስት ወራት የጡረታ መዋጮ ሂሳብ ከሚጠበቅበት ከሐምሌ 1 ቀን 2012 ጀምሮ እንዲከፍሉ የክፍያ ሽግሽግ ማድረግን በተመለከተ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማስፈፀሚያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ላይ በመወያየት ስራ ላይ እንዲውል ወስኗል።

ምክር ቤቱ በገንዘብ ሚኒስቴር የቀረቡትን የተለያዩ የብድር ስምምነቶችና የማጽደቂያ ረቂቅ አዋጆች ላይ ተወያይቷል።

ከብድሮቹ ከጃፓን ዓለም አቀፍ የትብብር ኤጀንሲ ጋር የተፈረመውን ለጅማ-ጭዳ እና ሶዶ-ሳውላ የመንገድ ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ፤ ከጣሊያን መንግስት ጋር የተፈረመውን የጤና ዘርፍ የልማት ግቦች ፕሮግራም ማስፈጸሚያ፤ ከጣሊያን መንግስት ጋር የተፈረመውን የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ክህሎት ማሻሻያናና የስራ ፈጠራ ፕሮግራም ማስፈጸሚያ ብድሮች ይገኙበታል።

በተጨማሪም ከኮሪያ ኢምፖርት ኤክስፖርት ባንክ ጋር የተፈረመውን የአዲስ አበባ ከተማ ፈጣን አውቶቡስ መስመር ግንባታ ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ፤ ከኮሪያ ኢምፖርት ኤክስፖርት ባንክ ጋር የተፈረመውን ለመሬት መረጃ አስተዳደር ስርዓት ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ እንዲሁም ከተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች የከሊፋ ፈንድ ለድርጅት ልማት ጋር አነስተኛና መካከለኛ ድርጅቶች የብድር አቅርቦት ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የሚውሉ ብድሮች ምክር ቤቱ ተመልክቷል።

ብድሮቹ ከአገሪቱ የብድር አስተዳደር ስትራቴጂ ጋር የሚጣጣሙ፣ በረዥም ጊዜ የሚከፈሉ፣ ከአንድ በመቶ በታች ወለድ የሚከፈልባቸውና ረዘም ያለ የእፎይታ ጊዜ ያላቸው መሆኑን ግምት ውስጥ በማስገባት የብድር ስምምነቶቹ ይጸድቁ ዘንድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፉ ተወስኗል።