አትሌቶች የ5 መቶ ሺህ ዶላር ድጋፍ ሊደረግላቸው ነው

77

አዲስ አበባ ሚያዚያ 20/2012(አዜአ)ኢበዓለም አቀፍ ደረጃ በተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ለተጎዱ አትሌቶች የ5 መቶ ሺህ ዶላር ድጋፍ ሊደረግላቸው ነው።

ድጋፉን የሚያደርጉት የዓለም አትሌቲክስና ዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ፋውንዴንሽን ናቸው።

የዓለም አትሌቲከስ ፕሬዚዳንት ሰባስቲያን ኮ እንደተናገሩት ድጋፉን የሚያገኙት በወረርሽኙ ምክንያት ባለፉት ወራት ውድድሮች ባለማድረጋቸው ገቢ ያጡ ፕሮፌሽናል አትሌቶች ነው።

ድርጅቱ ድጋፉን የሚያደርገው እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2020ና በ2021 በጀቱ በመቀነስ እንደሆነም የዓለም አትሌቲክስ ዘገባ ያመለክታል።

ድጋፉ በፕሬዚዳንቱ በሚመራው የባለሙያዎች ጥናት ቡድን ከተደረገበት በኋላ በስድስት ክፍለ አህጉራዊ የአትሌቲክስ ማህበራት አማካይነት እንደሚከፋፍል ድርጅቱ አስታውቋል።

በቡድኑ ውስጥ ከተካተቱ አባላት መካከል የኦሎምፒክና የዓለም የ1ሺህ 500 ሜትር ሻምፒዮናው ሞሮኳዊው ሂሻም አልግሩዥ ይገኝበታል።

አልግሩዥ በሰጠው አስተያየት ወረርሽኙ በሁም የኅብረተስብ ክፍሎች ላይ እያደረሰ ያለው ኢኮኖሚያዊ ጉዳት አትሌቶችም ከውድድሮች የሚያገኙት የገንዘብ ሽልማት በመቅረቱ ተጎጂ መሆናቸውን ተናግሯል።

ይህንን ሁኔታ ለመቀየር እርስ በርስና መተረዳዳት የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ እገዛ እንደሚያስፈልግ ገልጾ፣አትሌቶች በዘላቂነት የሚደገፉበት ፈንድ ማቋቋም እንደሚያስፈልግ አመልክቷል።

ቡድኑ በዚህ ሳምንት በሚያደርገው ውይይት አትሌቶቹን የሚደገፉባቸው ተጨማሪ ስልቶች እንደሚያፈላልግ የድርጅቱ መረጃ ይገልጻል።

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ዓለም አቀፍ ውድድሮች በመቋረጣቸው ኑሮአቸውን ለመምራት እየተቸገሩ መሆናቸውን እየገለጹ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንም ችግሩ ዓለም አቀፍ በመሆኑ ለመፍታት መቸገሩን ሲገልጽ  ነበር።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም