በኢትዮጵያ የተፈጥሮ ጋዝ ማቀነባበሪያ ግንባታ የጥናት ስምምነት ተፈረመ

452

አዲስ አበባ ሚያዚያ 20/2012(ኢዜአ) የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር በኢትዮጵያ የተፈጥሮ ጋዝ ማቀነባበሪያ ለመገንባት የሚያስችለውን የጥናት ስምምነት ከአሜሪካው ግሪንኮም ቴክኖሎጂስ ጋር ዛሬ ተፈራርሟል።

በሶማሌ ክልል ኤልኩራን አካባቢ የተገኘውን የተፈጥሮ ጋዝ ጥቅም ላይ ለማዋል የተለያዩ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ይገኛሉ።

በቅርቡ የተፈጥሮ ጋዝን ማልማት የሚያስችል የተፈጥሮ ጋዝ ንግድ ስምምነት መፈረሙ ይታወቃል።

ዛሬ የተደረገው ስምምነትም የተፈጥሮ ጋዝን ወደ ፈሳሽና ሌሎች ለኢንዱስትሪና ፔትሮ ኬሚካል ግብዓትነት ወደ ሚያገለግሉ ይዘቶች ለመቀየር የሚያስችል ፋብሪካና ቴክኖሎጂ በኢትዮጵያ ለማቋቋም የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል።

በሚኒስቴሩ የነዳጅ ልማትና ፍለጋ ፈቃድ ዳይሬክተር ዶክተር ቀጸላ ታደሰ እንደገለጹት፤ ለፕሮጀክቱ የአንድ አመት የጥናት ጊዜ ተሰጥቷል።

የፋብሪካው ግንባታ እንደ ቤንዚን፣ ነጭ ጋዝ፣ ዲዝል እና ሌሎችንም ለማምረትና ከውጭ ወደ አገር ውስጥ የሚገባውን የነዳጅ ውጤት ለመተካት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል።

ግሪንኮም ቴክኖሎጂስ ከሃዩንዳይ ኢንጅነሪንግ ኤንድ ኮንስትራክሽን ጋር በመሆን ለሚያከናውኑት ለዚህ ፕሮጀክት ከ3 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር በላይ በጀት ተይዞለታል።

ለጥናቱ የሚያስፈልገው 70 ሚሊዮን ዶላር በግሪንኮም ቴክኖሎጂስ ኩባንያ የሚሸፈን እንደሚሆንም ተገልጿል።

የግሪንኮም ቴክኖሎጂስ ኩባንያ ማናጀር ኢማኑኤል መኩሪያ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ አገሪቱ ለተለያዩ አገልግሎቶች የምታውለውን የነዳጅ ፍላጎት የምታሟላው ከውጭ በማስገባት ነው።  

ፕሮጀክቱ የውጭ ምንዛሬ በማዳን ከፍተኛ ገንዘብ እንደሚያስገኝና የቴክኖሎጂና የእውቀት ሽግግር በመፍጠር የአገሪቱን የነዳጅ ኢንዱስትሪ በማነቃቃት ረገድ ትልቅ ሚና እንዳለውም ገልጸዋል።

ለ10 ሺህ ጊዜያዊና ለ300 ቋሚና ከፍተኛ ባለሙያዎች የስራ እድል የሚፈጥር መሆኑንም ጠቁመዋል።

ጥናቱን ለማጠናቀቅ የ12 ወራት የጊዜ ገደብ የተያዘ ሲሆን አጠቃላይ ጥናቱ ተጠናቆ ወደ ተግባር ለመግባትም እስከ 24 ወራት እንደሚፈጅ ነው የተገለጸው።

የሚገነባው የማቀነባበሪያ ፋብሪካ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የተፈጥሮ ጋዝን ወደ ተለያዩ ይዘቶች የሚቀይር ሲሆን ናፍጣ፣ የአውሮፕላን ነዳጅ እና ለውበት መጠበቂያ አምራቾች ግብአት የሚያገለግሉምርቶችን የሚያቀናብር መሆኑ ተጠቁሟል።

የግብርና፣ የጤና፣ የኮንስትራክሽንና የኢንፎርሜሽን ኮሚኒኬሽን ኢንዱስትሪዎች በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ወደ አገር ውስጥ የሚያስገቧቸውንና ለምርት ሂደት የሚጠቀሙባቸውን ግብአቶች በአገር ውስጥ እንዲያገኙ ለማድረግም ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል ተብሏል።

በሌላ በኩል ዛሬ በተፈረመ ሌላ ስምምነት በትግራይ ክልል፣ ምዕራብ ትግራይ ዞን፣ ታህታይ አዲአቦ የኳርትዝ ማዕድን ፍለጋ ፈቃድ ተሰጥቷል።

ይህም የቆዳ ስፋቱ 198 ሺህ 695 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የሚከናወን መሆኑ ተገልጿል።

ለ3 ዓመታት የሚፀናው ይህ ስምምነት ለ33 ኢትዮጵያውያን የስራ ዕድል የሚፈጥርና 6 ሚሊዮን ብር የኢንቨስትመንት ካፒታል ተይዞለታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም