ኢትዮጵያ በአንበጣ መንጋ 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል ምርት አጥታለች

486

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 20/2012 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ በአንበጣ መንጋ 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ማጣቷን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

የግብርና ሚኒስቴር የሰብል ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሳኒ ረዲ ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንዳመለከቱት ካለፈው ሰኔ አጋማሽ ጀምሮ የተከሰተው መንጋ በ198 ሺህ በሚደርስ መሬት ላይ የነበረ ሰብል ጉዳት አድርሷል።

በስድስት ክልሎችና በአንድ የከተማ አስተዳደር 170 ወረዳዎች የነበረ የበቆሎ፣የማሽላና የስንዴ ሰብል በመንጋው ጉዳት እንደደረሰበት አስረድተዋል።

መንጋውን በ260ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ኬሚካል በመርጨት መከላከል እንደተቻለም አቶ ሳኒ አመልክተዋል።

በዚህም የየአካባቢውን የሰው ኃይል በማንቀሳቀስና ለጋሽ አካላት ድጋፍ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ የሚከሰተውን ችግር ለመፍታትና በቴክኖሎጂ የተደገፈ አሰራር ለማጠናከር ተጨማሪ ተሽከርካሪዎችን ጥቅም ላይ እንደሚውሉ ገልጸዋል።

ከዓለም ባንክም 63 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ለማግኘት እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

አርሶ አደሩም በአካባቢያቸው መንጋው ሲከሰት ሪፖርት በማድረግና ማሳቸውን ከመንጋው እንዲከላከሉ ሚኒስትር ዴኤታው አሳስበዋል።

መንጋው እስከ ጥቅምት 2013 እንደሚኖር ትንበያዎች እንደሚያመላክቱ ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅትም በደቡብ፣በኦሮሚያ፣ በሶማሌና አፋር አንዳንድ አካባቢዎች የተከሰተውን መንጋ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

መንጋው በሰብል ላይ ያደረሰውን ጉዳትና በቀጣይ የሚያደርሰውን ጉዳት በተመለከተ ከአደጋ ስጋትና ሥራ አመራር ኮሚሽንና ከዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት በመቀናጀት ጥናት መደረጉንም ገልጸዋል።