በኢትዮጵያ በኮቪድ-19 ሊያጋጥም የሚችለውን የኢኮኖሚ ጫና ለመቋቋም የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ ነው

128

አዲስ አበባ ፣ሚያዚያ 20/2012(ኢዜአ) በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አዘጋጅነት "ፈጠራ በቀውስ ጊዜ" በሚል ርእስ የአዲስ ወግ ዌቢናር በቴክኖሎጂ በመታገዝ በቪዲዮ ኮንፍራንስ ተካሂዷል።

የኮሮናቫይረስ ወርርሽኝ በዓለም ላይ እየተስፋፋ መመጣቱን ተከትሎ በኢትዮጵያም ሊያጋጥም የሚችለውን የኢኮኖሚ ጫና ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ ተግባራት መጀመራቸውን የፕላንና ልማት ኮሚሽን ኮሚሺነር ዶክተር ፍጹም አሰፋ ተናገሩ።

አዲስ ወግ አንድ ጉዳይ በዛሬው ውይይቱ በቪዲዮ ኮንፍረንስ ዌቢናር የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የሚያመጣውን ተጽዕኖ ተከትሎ ለመጭው ጊዜ ፈጠራ የታከለበት መፍትሔ ማፈላለግ ዙሪያ ትኩረቱን አድርጎ መክሯለ። 

በዌቢናሩ ውይይት ላይ የፕላንና ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ፍፁም አሰፋን ጨምሮ የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር አብረሃም በላይ፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የታሪክ ምሁር ዶክተር ታምራት ሀይሌ፣ ከኢትዮ ጆብስ አቶ የሱፍ ረጃህ፣ የስነ ልቦና ባለሙያ ሰብለ ሀይሉ እና አቶ ቴድሮስ ታደሰ ተካፍለዋል። 

በውይይቱም ዶክተር ፍፁም እንደገለጹት አጋጣሚው ከፍተኛ የሆነ የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ የሚያመጣና አንዳንዶቹን ሴክቶሮች መልሰው እንዳያገግሙ ሊያደርግ የሚችል ነው።

ለዚህም በተለይ ኢኮኖሚውን ለማዳን የአገሪቷን የኢኮኖሚ አውድ ባማከለ ሁኔታ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት እየተሰራ ነው ብለዋል።

ኢኮኖሚውን ለማነቃቃትና ዝቅተኛ ወደ ሆነ መነሻ እንዳይንሸራተት ወደ 15 ቢሊዮን የሚሆን ገንዘብ በብሄራዊ ባንክ በኩል ወደ ግል ባንኮች ፈሰስ መደረጉንም ጠቅሰዋል።

በኢኮኖሚ መቀዛቀዝ በከፍተኛ ሁኔታ ሊጎዱ የሚችሉ ሴክተሮችም ብድር እንዲመቻችላቸውና ብድራቸውን የመክፈያ ጊዜም እንዲራዘምላቸው እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

የጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማትም  በከፍተኛ ሁኔታ ብዙ ቤተሰብንና ሰራተኞችን  የያዙ እንደመሆናቸው በቅርብ በተደረጉ ውሳኔዎች ብደር የሚያገኙባቸው ሁኔዎች መመቻቸቱንም ኮሚሽነሯ ገልጸዋል።

ለጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት መንግስትም ሆነ ግለሰቦች የቤት ኪራይ ማሻሻያ እንዲያደርጉ፣ኢክስፖርትን የማበረታታት የስራ ግብርንም ሆነ የትርፍ ግብርን የሚመለከቱ ማበረታቻዎች እየተደረጉ መሆኑን አብራርተዋል።

አዳዲስ የፈጠራ ሃሳቦችን ለሚያመጡ የፈጠራ ስራ ላይ ለተሰማሩትም የገንዘብና ሌሎች ድጋፎች ተመቻችተዋል ብለዋል።

እንዲህ ያሉ የችግር ጊዜያትን ለመቋቋም ሆነ ለዘላቂ የኢኮኖሚ ግንባታ የወጣቱን ኃይል መጠቀም እንደሚገባ በውይይቱ ወቅት ተነስቷል።

የኮቨድ-19 አጋጣሚ ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ ቀውስ የሚያስከትል በመሆኑ ወጣቶች በስፋት ወደ ስራ ፈጣሪነት እንዲገቡ እገዛ ሊደረግላቸው ይገባልም ተብሏል።

በኢትዮጵያ 25 ሚሊዮን ገደማ የሚሆኑ ህዝቦቿ ከድህነት ወለል በታች የሚኖሩ በመሆናቸው የወጣቶች ስራ ፈጠራና የስራ ተነሳሽነት ቁልፍ ጉዳይ መሆኑም ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም