ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ በዩኔስኮ ዓለም አቀፍ ስብሰባ ላይ ተሳተፉ

117

አዲስ አበባ ፤ሚያዚያ 19/2012 (ኢዜአ) የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ በቪዲዮ ኮንፈረንስ በተካሄደው የዩኔስኮ ዓለም አቀፍ ስብሰባ ተሳተፉ።

የፕሬዝዳንት ፅህፈት ቤት እንዳመለከተው ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ የወደፊት የትምህርት ዕጣ ፈንታን በሚመለከተው ዓለም አቀፉ የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጀት /ዩኔስኮ/ ዓለም አቀፍ ኮሚሽን ሁለተኛ ስብሰባ ነው የተሳተፉት።

በተደረገው ስብሰባም ኮሮናቫይረስ በትምህርትና ልማት ላይ በረጅም ጊዜ ሊያስከትል የሚችለውን ተፅዕኖ ለመከላከል የፖሊሲ ምክረ ሀሳብ ለማዘጋጀት መግባባት ላይ መደረሱ ተገልጿል።

በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ሳቢያ ከመጀመሪያ ደረጃ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በመዘጋታቸው በዓለም ላይ ከ 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው ተስተጓጉለዋል።

በዩኔስኮ አነሳሽነት የተቋቋመው የሉላዊ የትምህርት ጥምረት አካታች የህጻናት ታዳጊዎች ትምህርት ስርዓት ለመዘርጋት ጥረት እያደረገ ይገኛል።

የርቀት ትምህርት በወረርሽኙ የተስተጓጎለውን የመማር ማስተማር ችግር በአፋጣኝ ለማጥበብ ብሎም ግልጽና ተለዋዋጭ የትምህርት ስርዓት ለመዘርጋት ስለሚረዳ እንደ አማራጭ ተቀምጧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም