የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ተመራቂ ተማሪዎች ደም ለገሱ

99
ሶዶ ሰኔ 26/2010 የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የዘንድሮ ተመራቂ ተማሪዎች ደም ለገሱ፡፡ ተማሪዎቹ የደም ልገሳ ዛሬ ያካሄዱት በሶዶ ማረሚያ ተቋም በመገኘት ሲሆን አቅምና ጠያቂ ለሌላቸው ታራሚዎችም የአልባሳት ድጋፍ አድርገዋል፡፡ የተመራቂ ተማሪዎች ተወካይ እጩ ዶክተር ኤልዳና ዳዊት የደም ልገሳ ያደረጉት ጉዳት ደርሶባቸው በደም እጦት ምክንያት የሚሞቱትን ለማዳን በሚል መሆኑን ተናግራለች፡፡ "ታራሚዎች ለሕክምና ወደጤና ተቋማት ሲመጡ ሰፊ የጤና ትምህርት የማግኘት ዕድል የላቸውም" ያለችው ተመራቂዋ በበጎ ፈቃደኝነት የተለያዩ ጤና ነክ ትምህርቶችን ለታራሚዎች ከመስጠት ባለፈ የተለያዩ አልባሳትን አቅም ለሌላቸው መለገሳቸውን ገልጻለች፡፡ እንደ ዶክተር ኤልዳና ገለጻ፣ አገራዊ አንድነት ላይ መንግስትን ከመደገፍ አንጻር የድርሻቸውን ለመወጣት ሲሉ ያደረጉትን የደም ልገሳ  ታራሚዎች ከማረሚያ ቤት ሲወጡ የልማቱ አጋር እንዲሆኑ ለማነሳሳት በሚል መርሀ ግብሩን በማረሚያ ቤቱ ማዘጋጀታቸውን ገልጻለች፡፡ " በበጎ ተግባራት መሳተፍ ከምንም በላይ መንፈሳዊና አዕምሯዊ እርካታን ይሰጣል" ያለው ደግሞ ደም ሲለግሱ ከነበሩት መካከል ሌላው እጩ ተመራቂ ዶክተር ፍሬው ዳንኤል ነው፡፡ በአገሪቱ የተፈጠረውን የአንድነትና አገራዊ ስሜት ለመደገፍ ባለፈው ሰኔ 16 ቀን 2010ዓ.ም ለሰልፍ አደባባይ በወጡ ዜጎች ላይ በተፈጸመ የቦምብ ጥቃት አደጋ ለደረሳቸው ወገኖች ድጋፋቸውን ለመግለጽ ሲሉ ደም መለገሳቸውን ተናግሯል፡፡ የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ኮሙኒኬሽንና የህዝብ ግንኙነት ሥራ ሂደት አስተባባሪና የኮሌጁ ተወካይ አቶ ማቴዎስ ጭናሾ በበኩላቸው የደም ልገሳው የተዘጋጀው በመስቀል አደባባይ የደረሰውን አደጋ ለማውገዝና ለተጎዱ ዜጎች ድጋፍ ለማድረግ መሆኑን ገልጸዋል። ከእዚህ በተጨማሪ በሃዋሳና አካባቢ ተከስቶ በነበረው የጸጥታ ችግር ምክንያት ተፈናቅለው በጤና ችግር ላይ ያሉ ወገኖችን በተለይም ለእናቶችንና ለህጻናት ደም እንዲደርስ በማሰብ ጭምር መሆኑን አመልክተዋል፡፡ "በሃዋሳ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ኮሌጁ የጤና ባለሙያዎችን በመላክ በሽታን ከመከላከልና ስነ ልቦና ከመመለስ አንጻር እየሰራ ነው" ያሉት አቶ ማቴዎስ፣ የኮሌጁ ሠራተኞች ከሰኔ ወር ደመወዛቸው 3 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ መስጠታቸውንም ተናግረዋል፡፡ የሶዶ ማረሚያ ተቋም ኃላፊ ተወካይ ኮማንደር ፈቃዱ መኮንን በበኩላቸው "የኮሌጁ ተማሪዎቹ ታራሚዎችን በትምህርትና በቁሳቁስ ለመርዳት ማሰባቸው የእርስ በርስ መረዳዳት መገለጫና የሚያኮራ ተግባር ነው" ብለዋል፡፡ የደም ልገሳ መርሀ ግብሩ አገራዊ እንድነትና የእርስ በርስ መተሳሰብን ለማጠናከር ያለው ፋይዳ የጎላ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ የደም ልገሳ መርሀ ግብሩን ያዘጃጉት 71 የኮሌጁ ተማሪዎች በተቋሙ ለተከታታይ ስድስት ዓመታት ትምህርታቸውን ተከታትለው ያጠናቀቁ ሲሆኑ በመጪው ቅዳሜም በዶክትሬት ዲግሪ ይመረቃሉ፡፡ የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በዶክትሬት ዲግሪ ደረጃ ተማሪዎችን ሲያስመርቅ ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑ ታውቋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም