የተፈናቀሉትን ለመመለስ በአገር ሽማግሌዎች እየተሰራ ያለው ስራ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት....ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል

65
ሀዋሳ/ሶዶ ሰኔ 26/2010 በሲዳማ ዞን ሃዋሳ ዙሪያ ወረዳ በተፈጠረ ሁከት ምክንያት ከመኖሪያ ቤታቸው የተፈናቀሉትን ለመመለስ በአገር ሽማግሌዎች እየተሰራ ያለው ስራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የደኢህዴን ሊቀመንበርና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል አሳሰቡ፡፡ አፈ ጉባኤዋ በሃዋሳ ዙሪያ ወረዳ ሻመና ቀበሌ ከተጠለሉ ተፈናቃዮች ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል በውይይቱ ላይ እንዳሉት የክልሉ መንግስትና ደኢህዴን በተፈጠረው ችግር ለደረሰው ጉዳት የተሰማቸውን ሀዘን ገልጸዋል፡፡ የሲዳማና የወላይታ ህዝቦች አንዳቸው ከአንዳቸው የተጋቡና ጠንካራ ትስስር ያላቸው ህዝቦች በመሆናቸው በመካከላቸው ማንም ጣልቃ መግባት እንደሌለበት ተናግረዋል፡፡ የቆየውን የአብሮነት ስሜት ለመመለስ የሁለቱ ህዝቦች የአገር ሽማግሌዎች ለጀመሩት ሰላም የማስፈን ሥራ የክልሉ መንግስትና መሪ ድርጅቱ ደኢህዴን አድናቆት እንዳላቸው ገልጸው፣ የተጀመረው ሥራ እንዲጠናከር አስገንዝበዋል፡፡ በሁለቱ ህዝቦች መካከል ተከስቶ ለነበረው አለመግባባት ሰላምን የማይፈልጉ ኃይሎች ሴራ እንጂ ሁለቱንም ህዝብ እንደማይወክል ገልጸዋል። ወይዘሮ ሙፈሪያት ህዝቦችን ሰላም ለመንሳትና ለማቃቃር የሚጥር አካልን ወደህግ ለማምጣት በመንግስት በኩል ለሚደረገው ክትትል ህዝቡ ትብብር በማድረግ የሚጠበቅበትን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በተፈጠረው ችግር ምክንያት ተፈናቅለው በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ አርሲ ዞን ሲራሮ ወረዳ የሰፈሩ ጭምር ወደ መኖሪያ ስፍራቸው እንዲመለሱ የማድረግ ስራ በፍጥነት መከናወን እንዳለበትም አመልክተዋል፡፡ በወረዳው የሻመና ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ አበራሽ ዴቻሞ በበኩላቸው ከተፈናቀሉበት ጊዜ ጀምሮ የዕለት ደራሽ እርዳታ በቀይመስቀልና በሃይማኖት መሪዎች በኩል እያገኙ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ በተጠለሉበት ትምህርት ቤት አረጋዊያን፣ ህጻናት፣ ነፍሰጡርና አራስ እናቶች መኖራቸውን ጠቁመው ለእነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚቀርበው ምግብ የተመጣጠነ ባለመሆኑ ለጉዳት እየተዳረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ሌላው ከእዚሁ ቀበሌ የተፈናቀሉትና ጡረተኛ የሆኑት አቶ ዮሐንስ ቦሻሼ በበኩላቸው ሁለቱ ህዝቦች በጋብቻ የተሳሰሩና ለረጅም ዓመታት አብረው የኖሩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ "የኔን ልጅ ያገባት የሲዳማ ተወላጅ ነው" በማለትም ሁለቱ ህዝቦች ተቀላቅለው የሚኖሩ ህዝቦች መሆናቸውን ተናግረዋል። በሻመና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከተጠለሉ ተፈናቃዮች ጋር በመምከር እርቅ ለማውረድ በስፍራው የተገኙት የሲዳማ ብሔር የአገር ሽማግሌ አቶ ገልፈቶ ግዴሳ ሁለቱ "ለረጅም ዓመታት በጋራ የኖርን፣ አብረን የምንበላና አብረን የምንጠጣ ህዘቦች ነን" ብለዋል፡፡ "የእኛ ህዝብ ከወላይታ ህዝብ ጋር እንደዚህ አይነት ጥል ይፈጥራል የሚል እምነት አልነበረንም፤ ሁለታችንም እንደአንድ ህዝብና አንድ አካል ሆነን ነው የኖርነው" ሲሉም ገልጸዋል፡፡ ተከስቶ በነበረው ግጭት ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸውና የተፈናቀሉ ወገኖች ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ ለማድረግ እየመከሩ መሆናቸውንና በነገው ዕለትም እርቅ ለማውረድ ቀጠሮ መያዛቸውን ተናግረዋል፡፡ በተያያዘ ዜና ከሀዋሳ ዙሪያ ወረዳ ወደ ኦሮሚያ ክልል ሲራሮ ወረዳ ለተፈናቀሉ ዜጎች የወላይታ ዞን 3 መቶ ሺህ ብር የሚያወጣ አልባሳትና የተለያዩ የምግብ ማብሰያ ቁሳቁሶችን ድጋፍ አድርጓል፡፡ የዞኑን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አስራት ጤራን ጨምሮ የዞኑ አመራሮች ትናንት በስፍራው ተገኝተው ተፈናቃዮቹን በመጎብኘት አጽናንተዋል፡፡ ተፈናቃዮቹ ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግስትና ከአካባቢው ነዋሪዎች ለተደረገላቸው ድጋፍ አመስግነዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም