በቦንብ ጥቃት ለተጎዱ ዜጎች 100 ዩኒት ደም ተለገሰ

92
ደብረብርሃን ሰኔ 26/2010 የጠቅላይ ሚኒስትሩን የለውጥ እንቅስቃሴ ለመደገፍ በቅርቡ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ተካሄዱ በነበረው የድጋፍ ሰልፍ ላይ በደረሰው የቦንብ ጥቃት ለተጎዱ ዜጎች 100 ዩኒት ደም መለገሱን የደብረ ብርሃን ደም ባንክ አስታወቀ። በደም ባንኩ የደም ለጋሾች አስተባባሪ አቶ ሰለሞን እሸቴ ለኢዜአ እንደገለጹት ደሙ የተለገሰው ከተለያዩ በጎ ፈቃደኛ ግለሰቦች ነው፡፡ በጎ ፈቃደኞቹ ደሙን የለገሱት የጠቅላይ ሚኒስትሩን የለውጥ እንቅስቃሴ ለመደገፍ ሰልፍ ወጥተው በረደሰው የቦንብ ጥቃት ለተጎዱት ዜጎች  አጋርነታቸውን ለማሳየት ነው። በኢትዮዽያ ሲቨል ሰርቨስ ዩንቨርስቲ ተመራቂ ተማሪ አቶ ፍቅረማሪያም ደጀኔ በሰጠው አስተያየት በሰለጠነ ዘመን የሰው ልጅ ሀሳቡን በነፃነት መግለጽ በሚችልበት ወቅት በተቃጣው የቦምብ ጥቃት ማዘኑን ተናግሯል። ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ የደም ልገሳ ማድረጉን  አስታውሶ  "አሁን ያደረገው ልገሳ ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጀመሩትን የለውጥ ሂደቶች ለመደገፍ ጭምር በመሆኑ ልዩ ያዳርገዋል "ብለዋል። በከተማው ሌላው ደም ለጋሽ የሆነችው የቀበሌ ሶስት ነዋሪው ወጣት እየሩሳሌም ጌትነት በበኩሏ "ዜጎች አንድነት፣ ሰላምና ፍቅር ለሰበከው መሪ የምስጋና ቀን ላይ ቦምብ መጣል ተገቢ አይደለም "ብላለች። በጥቃቱ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች  ደም ለግሶ ማትረፍ የሚያኮራ መሆኑን ጠቅሳ በቀጣይም የሚጠበቅባትን ሁሉ ለማበርከት ዝግጁ መሆኗን ተናግራለች፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም