በሃዋሳ በቴክኖሎጂ በመታገዝ መደበኛ ትምህርት መስጠት ተጀመረ

94

ሀዋሳ፤ ሚያዝያ 14/2012 ( ኢዜአ) ተማሪዎች መደበኛ ትምህርታቸውን በሬዲዮና በቴሌግራም እንዲከታተሉ በየትምህርት አይነቱ አጋዥ መርጃ ጽሑፎችን በማሰራጨት መጀመሩን የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ አስታወቀ።

የግል ትምህርት ቤቶች ክፍያ መጠየቅ ያለባቸው በሀገር አቀፍ ደረጃ በተቀመጠው መሰረት ሊሆን እንደሚገባም አሳስቧል።

የመምሪያው ሃላፊ አቶ ደስታ ዳንኤል በሰጡት መግለጫ እንዳሉት በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የተቋረጠው መደበኛ ትምህርት ከዛሬ ጀምሮ በቴሌግራምና በሬዲዮ መሰጠት ተጀምሯል።

ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ ሬዲዮ ጋር በመተባበር ዛሬ የተጀመረው ትምህርት ከስድስተኛ እስከ 12ኛ ክፍል ላሉ ተማሪዎች ነው።

ተማሪዎች ከንክኪ ነጻ በሆነ መልኩ ራሳቸውን እየጠበቁ በቤታቸው ሆነው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ያሳሰቡት ሀላፊው ከሬዲዮ በተጨማሪ ከ7ኛ አስከ 12ኛ ክፍል ላሉ ተማሪዎች በሁሉም የትምህርት አይነት በቴሌግራም አጋዥ መርጃ ጽሑፎች እንዲጫኑ መደረጉን አስታውቀዋል።

ወላጆች በቴሌግራም ሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያና ሀዋሳ ትምህርት በሚል ገብተው ጽሁፎችን በማውረድ ለልጆቻቸው እንዲሰጡና ክትትል እንዲያደርጉም አሳስበዋል።

በተጨማሪም ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ጥያቄዎች እንደሚጫኑ ጠቁመው ተማሪዎች በአግባቡ ትምህርታቸውን በቤት ውስጥ ሆነው መከታተል አለመከታተላቸውን ለማወቅ መተግበሪያ መዘጋጀቱንም ገልጸዋል።

በሚያነቡበት ጊዜ ያልገባቸውና ማብራሪያ የሚፈልጉባቸው ጥያቄዎች ሲኖሯቸው መምህሮቻቸውን በስልክ መጠየቅ እንደሚችሉም ጠቁመዋል።

በግል ትምህርት ቤቶች ከክፍያ ጋር በተያያዘ በሀገር አቀፍ ደረጃ በተወሰነው መሰረት ከ50 እስከ 70 በመቶ መብለጥ እንደሌለበትና ከወላጅ ኮሚቴ ጋር በመነጋገር በፍጥነት ለወላጆች እንዲያሳውቁም አሳስበዋል።

በተጨማሪም ማንኛውም ትምህርት ቤት ለመምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞች ደመወዝ በሰዓቱ መክፈል እንደሚኖርበት አስታውሰው ሰራተኛ መቀነስም ሆነ ማሰናበት እንደማይቻል አቶ ደስታ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም