በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የህክምና ባለሙያዎች በሀገር ቤት መስራት የሚችሉበት ሁኔታ እየተመቻቸ ነው

77
አዲስ አበባ ሰኔ 26/2010 በተለያዩ የውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የህክምና ባለሙያዎች ወደ ሀገር ቤት በመመለስ በሀገሪቱ የጤና ዘርፍ ልማት መሳተፍ የሚችሉበት ሁኔታ እየተመቻቸ መሆኑን ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቀ። በአሜሪካና አውሮፓ ሀገራት በሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የተቋቋመው የኢትዮ-አሜሪካ የሀኪሞች ቡድን ከሚኒስቴሩና ከኢትዮጵያ የማህፀን ሀኪሞች ማህበር ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የሁለት ቀናት አውደ ጥናት ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ ተጀምሯል። ለውይይቱ መነሻ የሆኑ ጥናታዊ ፅሁፎች የቀረቡበት አውደ ጥናቱ በሀገሪቱ ወቅታዊ የህክምና አገልግሎት አሰጣጥ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥቶ በመምከር ላይ ነው። ሚኒስትሩ ዶክተር አሚር አማን በዚሁ ወቅት  እንደተናገሩት በተለያዩ የውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን  በሙያቸው ሀገራቸው ውስጥ መስራት የሚችሉበትን ሁኔታ ለማመቻቸት በሚኒስቴሩ ስር ራሱን የቻለ ዳይሬክቶሬት ተቋቁሞ እንቅስቃሴ ተጀምሯል። ባለሙያዎቹ እውቀትና በሀገር ውስጥ የሌሉ የህክምና መሳሪያዎችን ይዘው በመምጣት በጤናው ዘርፍ መሰማራት የሚችሉበትን አመቺ ሁኔታ ለመፍጠር የአሰራር ማዕቀፍ እየተዘጋጀ መሆኑንም ገልፀዋል። በማእቀፉ መሰረት መንግስትና የግል ባለኃብቱ በጋራ በመሆን መሰረተ ልማትና የህንፃ ግንባታውን በማጠናቀቅ ከውጭ ሀገራት ለሚመለሱ የህክምና ባለሙያዎች እንደሚያቀርቡ ነው የገለፁት። በራሳቸው ግንባታ በማከናወን በዘርፉ ለመሰማራት ለሚፈልጉ ደግሞ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት የሚያግዝ አሰራር አንደሚዘረጋም ዶክተር አሚር አስታውቀዋል። በዚህ ረገድ  የኢትዮ-አሜሪካ ሀኪሞች ቡድን በኢትዮጵያ ያለውን የጤና አገልግሎት ጥራት ለማሻሻል የሚደረገውን ጥረት እንዲያግዙ ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል። ብቃት ያላቸው ሙያተኞችን ለማፍራት፣ የህክምና መሳሪያዎች አስተማማኝነትን ለማረጋገጥና አጠቃላይ የህክምና አገልግሎቱን ጥራት ለማስጠበቅ በሚደረገው ጥረት ቡድኑ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር ተቀራርቦ መስራት ይችላል ሲሉም አመልክተዋል። በአውደ ጥናቱ የሚነሱ ሃሳቦች በዘርፉ ያሉ ጥንካሬዎችን ለማስቀጠልና ችግሮችንም ለመፍታት ግብዓት ይሆናል ያሉት ዶክተር አሚር፤ በተለይ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎችን ችግር ለይቶ በመፍታት በሰው ኃብት ልማት በጋራ ለመስራት እንደሚረዳም ተናግረዋል። ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እና የኢትዮ-አሜሪካ ሀኪሞች ቡድን በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነትም በዛሬው እለት ፈርመዋል። በስምምነቱ መሰረትም የሀኪሞች ቡድኑ ለኢትዮጵያውያን የህክምና ባለሙያዎች በየአመቱ የሚሰጠውን ስልጠናና ትምህርት አንደሚያጠናክረው የቡድኑ የቦርድ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር ግርማ ተፈራ ገልፀዋል። እንደ ፕሮፌሰር ግርማ ገለጻ ቡድኑ በኢትዮጵያ ያለውን የጤና ልማት ዘርፍ ለመደገፍ አንድ ሆስፒታል በማስገንባት ላይ መሆኑን አስታውቀዋል። ከአጠቃላይ ህክምና በተጨማሪ የልብና የአጥንት ቀዶ ጥገና እንደዚሁም የካንሰር ህክምና አገልግሎት የሚሰጠው ሆስፒታሉ በአውሮፓዊያኑ 2021 ግንባታው ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል። የኢትዮ-አሜሪካ ሀኪሞች ቡድን እ.አ.አ በ2011 በ12 ሀኪሞች የተመሰረተ ሲሆን አሁን ከ300 በላይ አባላት አሉት።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም