በሰሜን ሸዋ ዞን አርሶ አደሮች የተፈጥሮ ማደበሪያ የመጠቀም ልምዳቸው እያደገ መምጣቱ ተጠቆመ

73
ፍቼ/ነቀምቴ ሰኔ 26/2010 በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የሚገኙ አርሶ አደሮች የተፈጥሮ ማደበሪያ የመጠቀም ልምዳቸው እያደገ መምጣቱን አየዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት አስታውቋል። የኦሮሚያ ምርጥ ዘር ኢንተርፕራይዝ የምዕራብ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ለተያዘው የመኸር እርሻው ከ50 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሩ ማሰራጨቱም ተገልጿል፡፡ በኦሮሚያ ክልል ግብርና ጽህፈት ቤቱ የግብዓትና ኤክስቴንሽን ቡድን መሪ አቶ ፍቅሩ ከበደ ለኢዜአ እንደገለጹት በዞኑ 13 ወረዳዎች የሚገኙ አርሶ አደሮች የተፈጥሮ ማዳበሪያ በማዘጋጀት የመጠቀም ልምዳቸው ካሦስት ዓመታት ወዲህ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ነው። በዘንድሮ ዓመት 171 ሺህ 657 አርሶ አደሮች ከእንስሳት ተረፈ ምርትና ከቅጠላ ቅጠል ብስባሽ ከ6 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ማዘጋጀታቸውን ገልጸዋል። የማዳበሪያ መጠንም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ2 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሜትር ከዩብ ብልጫ እንዳለው ጠቁመው ማዳበሪያው ከ572 ሺህ ሄክታር የሚበልጥ መሬት እንደሚያለማ አስረድተዋል። ለዚህም በየደረጃው የሚገኙ የግብርና ባለሙያዎች፣ የአመራሩና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ለአርሶ አደሮች ስልጠና መስጠታቸውና አስታውቀዋል። ከሦስት ዓመት በፊት ማደባሪያ አዘጋጅተው ይጠቀሙ የነበሩት 50 ሺህ የማይበልጡ አርሶአደሮች እንደነበሩ ያስታወሱት አቶ ፍቅሩ በአሁኑ ወቅት አብዛኞች አርሶ አደሮች የተፈጥሮ ማዳበሪያውን አዘጋጅተው እየተጠቀሙ መሆኑን ተናግረዋል። የደገም ወረዳ የአሊዶሮ ቀበሌ  አርሶ አደር ንጋቱ ጎንፋ በበኩላቸው በፋብሪካ እየተዘጋጀ የሚቀርበው ሰው ሰራሽ ማዳበሪያ በየጊዜው ዋጋው እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል። ይህን ወጪ ለመቀነስ የተፈጥሮ ማዳበሪያ የማዘጋጀት ልምዳቸውን ከዓመት ወደ ዓመት እያሻሻሉ መሆናቸውን ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅት በማሳቸው አካባቢ ያዘጋጁትን የተፈጥሮ ማዳበሪያ ከዘመናዊ ማደበሪያ ጋር ቀላቅለው ለጤፍ እርሻቸው በመጠቀም ላይ መሆናቸውን ገልፀዋል። ለላፉት ሦስት ዓመታት የተፈጥሮ ማዳበሪያን በሁለት ሄክታር መሬታቸው ላይ በተከታታይ እንደተጠቀሙ የተናገሩት የዚሁ ቀበሌ አርሶ አደር አርጋው ጭቅሳ በበኩላቸው የመሬታቸው ለምነትና ምርታማነት መጠበቁን ተናግረዋል። በተለይ አትክልትና ፍራፈሬ በሚያለሙበት ወቅት እጅግ ውጤታማ እንደሆነ ጠቁመው ሌሎች አርሶ አደሮችም በተመሳሳይ ሁኔታ ማዳበሪያውን ቢጠቀሙ ምርታማ እንደሚሆኑ መክረዋል። በግራር ጃርሶ ወረዳ የቶርባን አሼ ቀበሌ አርሶ አደር ነገዎ አለሙ በበኩላቸው በ16 ሜትር ኪዩብ የጀመሩት የማዳበሪያ ዝግጅት ሥራ በአሁኑ ወቅት ወደ 180 ሚትር ኪዩብ ማሳደጋቸውን ነው የገለጹት። የተፈጥሮ ማዳበሪያ ከአካባቢው ቁሳቁስ በቀላል ወጪ የሚያዘጋጁት ከመሆኑም በተጨማሪ አንድ ጊዜ በእርሻ መሬት ላይ ከተጨመረ ለተከታታይ ሦስት ዓመታት መሬቱን በማዳበር መርታማነትን እንደሚያሳድግ የገለፁት ደግሞ የዞኑ አፈርና እጽዋት በለሙያው አቶ ሰመኝ ደበሌ ናቸው። በተለይ የተፈጥሮ ማዳበሪያው ከዘመናዊ የፋብሪካ ማዳበሪያ ጋር በጥቂቱ ተቀላቀሎ ጥቅም ላይ ቢውል ለምርት እደገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል። በተመሳሳይ ዜና የኦሮሚያ ምርጥ ዘር ኢንተርፕራይዝ የምዕራብ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ለተያዘው የመኸር እርሻው ከ50 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሩ ማሰራጨቱን አስታውቋል፡፡ የኢንተርፕራይዙ የምዕራብ ኦሮሚያ ቅርንጫፍ ዳይሬክተር አቶ ፉፋ ሾሮ እንዳስታወቁት ለ2010/2011 የመኸር እርሻ 52 ሺህ 50 ኩንታል በኦሮሚያ ክልል ለሚገኙ ዞኖች ተከፋፍሏል፡፡ ለአርሶ አደሩ የተከፋፈሉት ምርጥ ዘሮች የተለያዩ የበቆሎ ዝርያዎች፣ አኩሪ አተር፣ ዳጉሣና ስንዴ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡ ለአርሶ አደሩ የተሰራጨው ዲቃላ የበቆሎ ምርጥ ዘር በአማካይ በሄክታር ከ60 እስከ 70 ኩንታል፣ አኩሪ አተር ከ15 እስከ 20፣ ስንዴ ከ40 እስከ 50 እና ዳጉሳ ከ15 እስከ 20 ኩንታል ምርት መስጠት የሚችሉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ በዘንድሮ ዓመት የተሰራጨው ምርጥ ዘር ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ17 ሺህ 50 ኩንታል ብልጫ ያለው መሆኑም ታውቋል፡፡ በዘንድሮው ዓመት የተሰራጨው ምርት ዘር ከ208 ሺህ 200 ሄክታር የሚበልጥ መሬት መሸፈን የሚችል መሆኑንም ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል ፡፡ አርሶ አደሩ ምርጥ ዘር የመጠቀም ልምድ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ በመጪው ዓመት ከዘንድሮው ዓመት በበለጠ የአርሶ አደሩን ፍላጎት ለማሟላት በምሥራቅ ወለጋ፣ በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ፣ በቡኖ በደሌ ዞኖችና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በካማሺ ዞን በ3ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የምርጥ ዘር ብዜት ሥራ እያካሄደ መሆኑን አቶ ፉፋ ገልጸዋል፡፡ አንዳንድ የዞኑ አርሶ አደሮች ምርጥ ዘሩ እንደ ፍላጎታቸው የቀረበላቸው መሆኑን ተናግረዋል። ከአርሶ አደሮቹ መካከል የዲጋ ወረዳ የአርጆ ጉዳቱ የገጠር ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አስፋው ዋቅጅራ 150 ኪሎ ግራም የበቆሎ ምርጥ ዘር በመጠቀም 5 ሄክታር መሬታቸውን በበቆሎ መዝራታቸውን ገልጸዋል፡፡ የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ ሌላው አርሶ አደር ለታ ቱጌም በበኩላቸው 25 ኪሎ ግራም የበቆሎ ምርጥ ዘር ሙሉ የግብርና ፓኬጅ በመጠቀም በአንድ ሄክታር መሬታቸው ላይ መዝራታቸውን ገልጸዋል፡፡ በዋዩ ቱቃ ወረዳ የጉቴ ገጠር ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ደረጀ ጥላሁን በበኩላቸው ምርጥ ዘር መጠቀም ከጀመሩ ዓመታት መቆጠሩን ገልጸው፤ በአሁኑ ወቅትም 12 ነጥብ 5 ኪሎ ግራም የበቆሎ ምርጥ ዘር በግማሽ ሄክታር መሬት ላይ መዝራታቸውን ተናግረዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም