በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ኃላፊነታቸውን አልተወጡም የተባሉ አራት የፀጥታ ኃላፊዎች ከስራቸው ታገዱ

129
አሶሳ ሰኔ 26/2010 በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ተከስቶ የነበረውን የፀጥታ ችግር ለመቆጣጠር ኃላፊነታቸውን በአግባቡ አልተወጡም የተባሉ አራት የፀጥታ ኃላፊዎች ከስራቸው ታግደው ጉዳያቸው እየተጣራ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን አስታወቁ፡፡ የክልሉ ፖሊስ አባላት በወሰዱት አላስፈላጊ እርምጃ የሰው ህይወትና ንብረት መጥፋቱን አመልክተዋል፡፡ ለዚህም ተጠያቂ ናቸው የተባሉት የክልሉ አስተዳደርና ፀጥታ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ኃላፊው፣ የፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነሩ እንዲሁም የክልሉ ልዩ ኃይል ፖሊስ መምሪያ ኃላፊና ምክትላቸው ከስራ ታግደው ጉዳያቸው እየተጣራ መሆኑን  ርዕሰ መስተዳድሩ  ዛሬ ለጋዜጠኞች ገልጸዋል፡፡ የጸጥታ ችግሩ ከመከሰቱ በፊትና በኋላ አስፈላጊው የጥንቃቄ ስራ ባለመሰራቱና የጸጥታ ኃይሉ በወሰደው ያልተገባ እርምጃ የሰው ህይወት በመጥፋቱና ጉዳት በመድረሱ ኃላፊዎቹ ላይ እርምጃው መወሰዱን አቶ አሻድሊ ተናግረዋል፡፡ ከዚህም ሌላ በተከሰተው የፀጥታ ችግር ተሳትፈዋል የተባሉ  54 ግለሰቦች ተይዘው ጉዳያቸው እየተጣራ እንደሚገኝ ያመለከቱት ርዕሰ መስተዳድሩ ከመካከላቸውም 11ዱ የክልሉ የፀጥታ መዋቅር አባላት መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡ በክልሉ አሶሳ፣ ሸርቆሌ አካባቢዎችና ማኦ ኮሞ ልዩ ወረዳ በተከሰተው የፀጥታ ችግር እስካሁን ድረስ የአስራ አራት ሰዎች ህይወት ማለፉንና አስራ አንድ ሰዎች ደግሞ በደረሰባቸው ጉዳት የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው እንደሚገኝ  ገልፀዋል፡፡ ርዕሰ መስተዳድሩ በክልሉ በተከሰተው የፀጥታ ችግር ለጠፋው የሰው ህይወትና የአካል ጉዳት እንዲሁም በደረሰው የንብረት ውድመት የክልሉን ህዝብ ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡ በፀጥታ ችግሩ ምክንያት የቤተሰብ አባሎቻቸውን ላጡ እንዲሁም የአካል ጉዳትና ንብረት ለወደመባቸው ዜጎች የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚደርግም አስታውቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም