ወረርሽኙን ለመከላከል የቴክኖሎጂ ውጤቶች ጥቅም ላይ እየዋሉ ነው

103

ሀዋሳ ሚያዝያ 8/2012. የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል የተሰሩ ችግር ፈቺ የቴክኖሎጂ ውጤቶች በስፋት ተመርተው ለህብረተሰቡ እንዲዳረሱ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ርስቱ ይርዳው ገለፁ ፡፡

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በደቡብ ክልል ቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ኢንስቲትዩትና በሌሎች ተቋማትና ኢንተርፕራይዞች የተመረቱ ወረርሽኙን የመከላከል  ስራን የሚያግዙ አዳዲስ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ጎብኝተዋል፡፡ 

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ርስቱ ይርዳው በዚህ ወቅት እንዳሉት ተቋማቱ የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል የሚያገለግሉ አዳዲስ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን አምርተው ለህብረተሰቡ ተደራሽ በማድረግ  ተልዕኳቸውን በተግባር እየፈፀሙ ነው ብለዋል ።

እነዚህ ችግር ፈቺ የሆኑ የፈጠራ ውጤቶች በኢንተርፕራይዞች አማካይነት በሥፋት ተመርተው ለህብረተሰቡና ለጤና ተቋማት በፍጥነት እንዲዳረሱ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል ፡፡ 

የደቡብ ክልል ቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ፈርሻ በበኩላቸው ኢንስቲትዩቱ የማህበረሰቡን ችግር የመፍታት ኃላፊነቱን ለመወጣት በሥሩ ባሉ ባለሙያዎች እግርን ብቻ በመጠቀም አገልግሎት የሚሰጡ የእጅ መታጠቢያዎችንና ጭንብሎችን ማምረቱን አስረድተዋል፡፡ 

ሌሎች ተቋማትም እነዚህን የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ማምረት እንዲችሉ የ“ኦን ላይን” ስልጠና እንደሚሰጥ የገለፁት አቶ ሰለሞን ምርቶቻችንን በስፋት ለማዳረስ ከክልል ቢሮዎችና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር እየሰራን ነው ብለዋል፡፡ 

ከቤተሰቦቼ ጋር በመሆን ወረርሽኙን ለመከላከል የበኩላችንን አሰተዋፅኦ ለማበርከት በየትኛውም ስፍራ በመገኘት ለአንድ ታካሚ ሙሉ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል የሞተር ሳይክል አምቡላንስ ሰርተናል ያለው ደግሞ የፍሬNድሺፕ ኤሌክትሮ ሜካኒካል ኢንተርፕራይዝ አባል የሆነው ወጣት ቢንያም አስራት ነው፡፡ 

ወጣት ቢንያም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት አምቡላንሱን በስፋት አምርተው ተደራሽ የማድረግ ዕቅድ እንዳላቸው አስረድቷል፡፡ 

በጉብኝቱ ላይ እግርን ብቻ በመጠቀም የሚሰሩ የእጅ መታጠቢያዎች፣ የሆስፒታል አልጋዎች፣ አፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብሎች፣ የሞተር ሳይክል አምቡላንስና ሌሎች ውጤቶች ለዕይታ ቀርበዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም