ኢንዱስትሪዎች በትንሳኤ በዓል ዋዜማ ከዋናው የኃይል ቋት የኤሌክትሪክ ኃይል እንዳይጠቀሙ ተጠየቀ

54

አዲስ አበባ ሚያዚያ 8/2012(ኢዜአ) የከፍተኛና የመካከለኛ ኃይል ተጠቃሚ ኢንዱስትሪዎች በመጪው የትንሳኤ በዓል ዋዜማ ከዋናው የኃይል ቋት የኤሌክትሪክ ኃይል እንዳይጠቀሙ ተጠየቀ።

የመኖሪያና የንግድ ቤት ተጠቃሚ ደንበኞችም ትላልቅ የማብሰያ ዕቃዎችን ከፍተኛ የኃይል ፍላጎት በሚበዛበት ሰዓት ባለመጠቀም የኃይል መጨናነቅ እንዲቀንስ የድርሻቸውን እንዲወጡም ጥሪ ቀርቧል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በመጪው እሁድ የሚከበረውን የትንሳኤ በዓል ምክንያት በማድረግ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ በዓሉ በተሳካ ሁኔታ እንዲያልፍ አስፈላጊ ዝግጅት ተደርጓል።

የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝን ለመግታት መንግስት እያደረገ ያለውን ጥረት በመደገፍ የኃይል አቅርቦቱ አስተማማኝ እንዲሆን ድርጅቱ ከሚያደርገው ጥረት በተጨማሪ ህብረተሰቡ የትንሣኤ በዓልን በተሳካ ሁኔታ እንዲያሳልፍ አስፈላጊ ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱን አስታውቋል። 

ከበዓሉ በፊት የኃይል መቆራረጥ የሚበዛባቸውን መስመሮችና አካባቢዎች በመለየት ኃይል የማመጣጠንና የቅድመ መከላከል ጥገና ሥራዎች ተከናውነዋል።

ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት ለሚፈጠር የኃይል መቋረጥ አስቸኳይ የጥገና ሥራ ለማከናወንም ዝግጅት መደረጉን ነው መግለጫው ያስታወቀው። 

ይህንን ሥራ በባለቤትነት የሚያስተባብሩና የሚያከናውኑ በኮርፖሬት ደረጃ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር በመተባበር ዐቢይ ኮሚቴና በክልል ደረጃ ንዑሳን ኮሜቴዎች ተዋቅረው ሥራ ጀምረዋል፡፡

ይሁንና ከዓቅም በላይ በሆነ ችግር በኤሌክትሪክ መስመሩ ላይ ከፍተኛ የኃይል መጨናነቅ ሊከሰት ስለሚችል የድንጋይ ወፍጮ፣ የፕላስቲክ፣ የጨርቃ ጨርቅ፣ የብረታ ብረት፣ የቆዳና ቆዳ ውጤቶች፣ የኬሚካልና ሌሎች የከፍተኛና የመካከለኛ ኃይል ተጠቃሚ ኢንዱስትሪዎች በበዓሉ ዋዜማ ከዋናው የኃይል ቋት ኤሌክትሪክ እንዳይጠቀሙ ተጠይቋል።

ሁሉም የመኖሪያና የንግድ ቤት ተጠቃሚ ደንበኞችም ትላልቅ የማብሰያ ዕቃዎቻቸውን ከፍተኛ የኃይል ጭነት በሚበዛበት ሰዓት እንዳይጠቀሙም ነው ድርጅቱ ያስታወቀው።

በተለይ በበዓሉ ዋዜማ ቅዳሜ ከቀኑ 10፡00 እስከ ምሽቱ 3፡00 ባለው ጊዜ ባለመጠቀም የኃይል መጨናነቅ እንዲቀንስ ደንበኞች የበኩላቸውን አስተዋጾ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል።

በአጠቃቀም ወቅት የኤሌክትሪክ አደጋ እንዳይፈጠር ህብረተሰቡ በኤሌክትሪክ መጠቀሚያ ዕቃዎችና ገመዶች ላይ ከፍተኛ ጫና እንዳይፈጠር ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግም አመልክቷል፡፡

ደንበኞች ከኤሌክትሪክ ጋር የተገናኙ መረጃዎችን ለመጠየቅ፣ የአደጋ ጥቆማዎችና ሌሎች አስተያየቶችን ለማቅረብ በአቅራቢያ ወደሚገኝ የአገልግሎት መስጫ ማዕከል በአካል በመገኘት ወይም በ905 ነፃ የጥሪ ማዕከል በመደወል ማሳወቅ እንደሚችሉም ተመልክቷል።


ኤሌክትሪክ በሚቋረጥበት ጊዜ የጥገና ሥራ ለማከናወን የተቋሙን መታወቂያ የያዙ ባለሙያዎች በተለያዩ አካባቢዎች ለሥራ ጉዳይ እንደሚንቀሳቀሱ ህብረተሰቡ ተገንዝቦ መሰረተ ልማቶች እኩይ ተግባር ባላቸው አካላት እንዳይሰረቁ ተገቢውን ጥበቃ እንዲያደርግም ጥሪ ቀርቧል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም