ኢትዮ ቴሌ ኮም አሰራሩን እንዲያሻሽል ተጠየቀ

210
ነገሌ ሰኔ 25/2010 ኢትዮ ቴሌ ኮም የሚሰጠው አገልግሎት ተደራሽ  ቢሆንም ያሉበትን የአሰራርና የጥራት መጓደል እንዲያሻሻል ተጠየቀ፡፡ በኢትዮ ቴሌ ኮም የደቡብ ሪጅን በነገሌ ከተማ  በአገልግሎት አሰጣጡ ችግሮችና መፍትሄው ዙሪያ ከደንበኞቹ ጋር ተወያይቷል፡፡ በውይይቱ ከተካፈሉት ደንበኞች መካከል የከተማው ቀበሌ ሶስት ነዋሪ  አቶ ግርማ ኃይሌ በሰጡት አስተያየት የኢትዮ ቴሌ ኮም አገልግሎት በአካባቢያቸው ተደራሽ ቢሆንም በጥራት መጓደል ምክንያት በተገቢው ተጠቃሚ መሆን እንዳልቻሉ ተናግረዋል፡፡ የኔትወርክ መቆራረጥ ፣የመደበኛና የሞባይል ስልክ ቀፎ  የመለዋወጫ የጥራት ችግር መገለጫዎቹ እንደሆኑም ጠቁመዋል፡፡ ኢትዮ ቴሌ ኮም በየዓመቱ ከደንበኞቹ ጋር በሚያደርገው ውይይት አስተያየቶችን ቢቀበልም እስካሁን መሰረታዊ ለውጥ እንዳላመጣም ነው ደንበኛው የተናገሩት ፡፡ ድርጅቱ አሰራሩን በማዘመን ለሚሸጣቸው እቃዎች ጥራት ያለው መለዋወጫ እንዲያቀርብና አሁን ያለውን የኔትወርክ መቆራረጥ ችግር እንዲፈታላቸውን ጠይቀዋል፡፡ የከተማው ቀበሌ አንድ ነዋሪ  አቶ አሰፋ ጃለታ በበኩላቸው የኢንተር ኔት መቆራረጥና የገመድ አልባ ስልክ አለመስራት የተለመደ  ችግር እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ በቂ የሞባይል ቀፎ አቅርቦትም  ሌላው ችግር መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ በየአካባቢው የስልክ ምሰሶዎች እየወደቁ የሞባይል አገልግሎት በየጊዜው እንደሚቋረጥ ያመለከቱት ደግሞ ሌላው የኢትዮ ቴሌኮም ደንበኛ  አቶ አደም ኢብራሂም  ናቸው፡፡ ድርጅቱ ለመሰረተ ልማቶች በቂ ጥበቃ እንዲያደርግ ብልሽቶች ፈጥነው እንዲጠገኑና ለደንበኞቹ የአገልግሎት አሰጣጡን እንዲያሻሽል ጠይቀዋል፡፡ በኢትዮ ቴሌ ኮም የደቡብ ሪጅን የቀጥታ ቻናል ማናጀር አቶ መፈክር ጥላሁን ለአገልግሎት  አሰጣጥ ጥራት  ዋናው ችግር የድርጅታቸው ቅንጅት አሰራር ጉድለት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻል ከሚመለከታቸው የመንግስት ተቋማት ጋር በመነጋገር ከሪጂኑ ደንበኞች ከተነሱ 131 ቅሬታዎች መካከል ለአብዛኛዎቹ ምላሽ መሰጠቱን አመልክተዋል፡፡ የደንበኞችን ቅሬታና ጥያቄ ወደሚቀበሉ 994 የስልክ መስመሮች በየወሩ እስከ 13 ሚሊዮን ለሚመጡ ጥሪዎች ከሁለት ቀን ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ምላሽ እየተሰጠ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡ ድርጅቱ የሞባይል ካርድ የዱቤ ሽያጭን ጨምሮ የኢንተር ኔት ፍጥነትን ለመጨመር የሞባይል ኔትወርክ መቆራረጡን ለማሻሻልና በተመጣጣኝ ክፍያ በቂ የስልክ ቀፎ ለማቅረብ ማቀዱንም አብራርተዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም