ኒውዚላንድና ኢትዮጵያ የእንስሳትን ምርታማነት ለማሳደግ በጋራ ይሰራሉ- በኢትዮጵያ የኒውዚላንድ አምባሳደር

64
አዲስ አበባ ሰኔ 25/2010 ኒውዚላንድና ኢትዮጵያ የእንስሳት ምርታማነት ለማሳደግ በጋራ እንደሚሰሩ በኢትዮጵያ የኒውዚላንድ አምባሳደር ማርክ ራምስደን ተናገሩ። የእንስሳትን ምርታማነት በማሳደግ ከእንስሳት የሚለቀቅ በካይ ጋዝ ቅነሳ ላይ የሚያተኩር አውደ ጥናት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው። በአውደ ጥናቱም በኢትዮጵያ የኒውዚላንድ አምባሳደርን ጨምሮ ከምስራቅ አፍሪካ የመጡ የዘርፉ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችና ከዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ምርምር ተቋማት የመጡ ተመራማሪዎች እንዲሁም ምሁራን ተሳታፊዎች ናቸው። ሳይንስና ቴክኖሎጂን በመጠቀም የእንስሳትን ቁጥር በመቀነስ ምርታማነትን መጨመር የሚቻልበትን ሂደት ለፖሊሲ አውጭዎች ማመላከት ደግሞ የአውደ ጥናቱ ዋነኛ ዓላማ መሆኑ ተገልጿል። በኢትዮጵያ የኒውዚላንድ አምባሳደር ማርክ ራምስደን ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በኒውዚላንድና ኢትዮጵያ ከሚለቁት በካይ ጋዝ ውስጥ ሰፊውን ድርሻ የሚይዘው የግብርናው ዘርፍ ነው። አገራቸው ሳይንስና ቴክኖጂን በመጠቀም የእንስሳት ምርታማነት መጨመር ላይ በትኩረት እየሰራች መሆኑን የጠቆሙት አምባሳደሩ፤ ኢትዮጵያ የእንስሳትን ምርታማነት ለማሳደግ በምታከናውነው ተግባር አገራቸው በጋራ አንደምትሰራ ገልጸዋል። የግብርናና እንስሳት ሃብት ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር ፍቃዱ በየነ በበኩላቸው በኢትዮጵያ የእንስሳት ምርታማነት ማነስ ጋር ተያይዞ የእንስሳት ቁጥር ላይ ትኩረት ማድረግ በስፋት ይስተዋላል። የአንስሳት ቁጥር መጨመር ደግሞ የ'ሚቴን ጋዝ' ልቀትን ከፍ እንደሚያደርግ የተናገሩት ፕሮፌሰር ፈቃዱ፤ የእንስሳትን ምርታማነት ከፍ በማድረግና አማራጭ የፕሮቲን ምንጮችን በመጠቀም ችግሩን መፍታት እንደሚገባ አውስተዋል። የኢትዮጵያ መንግስት ከዚህ አንጻር በዓለም አቀፍ ደረጃ የተቀመጡ የበካይ ጋዝ ቅነሳ ስትራቴጂዎችን ከአገራዊ ፖሊሲ ጋር በማጣጣም እየተገበረ መሆኑን ጠቁመው፤ በሁሉም ሴክተሮች እየተተገበረ ያለውን ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚን ለአብነት አንስተዋል። መንግስት በእንስሳት ምርታማነት የተሻለ ልምድ ካላቸው አገራት በተጨማሪ በዘርፉ የተሻለ ተሞክሮ ካላቸው የምርምር ተቋማት የሚገኘውን ልምድ ገቢራዊ እንደሚያደርግም ፕሮፌሰሩ ገልጸዋል። የበካይ ጋዝ ቅነሳ አተገባበር የምግብ ዋስትናና ምርታማነትን ባማከለ መልኩ እንደሚከናወንም አክለዋል። ኢትዮጵያ ከሁሉም ዘርፍ በዓመት በአጠቃላይ 150 ሚሊዮን ቶን ካርቦን ወደ ከባቢ አየር የምትለቅ ሲሆን፤ ከዚህም ውስጥ በደን ጭፍጨፋና ምንጣሮ ምክንያት የሚለቀቀው ከፍተኛውን ቁጥር ይይዛል። ኢትዮጵያ በአፍሪካ ካላት ከፍተኛ ቁጥር ያለው የእንስሳት ሃብት ጋር ተያይዞም በሚቴን ጋዝ ልቀት ተጠቃሽ አገር ናት።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም