በምዕራብ ሸዋ ዞን የወባ ወረርሽኝ እንዳይከሰት ለማድረግ መቻሉ ተጠቆመ

76
አምቦ ሰኔ 25/2010 በምዕራብ ሸዋ ዞን ሕብረተሰቡን ያሳተፈ የወባ መከላከል ሥራ በመሰራቱ የወባ ወረርሽኝ እንዳይከሰት ለማድረግ መቻሉን የዞኑ ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡ ከክረምቱ ዝናብ ጋር ተያይዞ ሊከሰቱ የሚችሉ ወባና መሰል በሽታዎችን አስቀድሞ ለመከላከል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑም ተመልክቷል፡፡ በጽህፈት ቤቱ የተላላፊ በሽታዎች ክትትልና ቁጥጥር ሥራ ፈጻሚ አቶ ሀዌራ ቶሌራ እንደገለጹት፣ በዞኑ ወባ በወረርሽኝ መልክ ተከስቶ ጉዳት እንዳያደርስ ማድረግ የተቻለው የሕብረተሰቡ ገንዛቤ ከጊዜ ወደጊዜ እያደገ በመምጣቱ ነው። አቶ ሀዌራ እንዳሉት ሕብረተሰቡ በአካባቢ ጽዳት፣ በፀረ ወባ ኬሚካል ርጭትና በአልጋ አጎበር አጠቃቀም ላይ በቂ ግንዛቤ እንዲጨብጥ ተደረጓል፡፡ በመሆኑም ለወባ ትንኝ መራቢያ ምቹ የሆኑ ረግረጋማና ውሃ ያቆሩ አካባቢዎችን ህብረተሰቡ ተከታትሎ የማድረቅና የማፋሰስ ሥራ በየጊዜው በማከናወን ራሱን ከወባ በሽታ ከመጠበቅ ባለፈ የወባ ስጋት እንዲቀንስ አስተዋፅኦ አበርክቷል። አቶ ሀዌራ እንዳሉት፣ እየተገባደደ ባለው በጀት ዓመት ነዋሪዎችን በማሳተፍ በዞኑ ወባማ በሆኑ አስር ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደር 56 ሺህ ስኩዬር ካሬ ሜትር ቦታ በማጽዳትና ረግረጋማ ቦታዎችን በማድረቅ የወባ ትንኝ እንዳይራባና እንዳይዛመት ማድረግ ተችሏል። ባለፈው ዓመት ወባማ በሆኑ 225 የገጠር ቀበሌዎች በሚገኙ 275 ሺህ የመኖሪያ ቤቶች ላይ የጸረ ወባ ኬሚካል ርጭት ተካሂዶ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ሀዌራ፣ ዘንድሮ በተመሳሳይ ወቅት ስጋቱ በመቀነሱ በ150 ሺህ ቤቶች ብቻ ርጭት መካሔዱን አስረድተዋል። አቶ ሃዌራ እንዳሉት የበሽታው ምልክት የታየባቸው ሰዎች በአፋጣኝ ወደ ጤና ጣቢያ እንዲሄዱ ስለሚደረግ በወባ በሽታ ምክንያት የሞተ ሰው የለም። የክረምቱን ዝናብ ተከትሎም ወባና ውሃ ወለድ በሽታዎች በወረርሽኝ መልክ እንዳይከሰቱ አስቀድሞ ለመከላከልና ከተከሰተም አስቸኳይ የሕክምና አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል፡፡ እንደ አቶ ሀዌራ ገለጻ፣ በዚህ ዓመት በወባ በሽታ ተይዘው ለሕክምና ወደ ጤና ተቋማት የመጡ ሰዎች ቁጥር ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ445 ቀንሷል፡፡ ሕብረተሰቡን በማንቀሳቀስ ወባን ለመከላከል በተደረገው ጥረት በዞኑ ከ400 ሺህ በላይ ሰዎችን ከበሽታው መጠበቅ እንደተቻለም አመልክተዋል። በወባ ቅድመ መከላከል ሥራ ከተሳተፉ የዞኑ ነዋሪዎች መካከል የጊንጪ  ከተማ ነዋሪ  ወይዘሮ አስቴር ዘሪሁን "በአካባቢያቸው የተጠናከረ የወባ መከላከልና ቁጥጥር ሥራ በመሰራቱ ከበሽታው ስጋት ነጻ ሆነናል" ብለዋል፡፡ ለወባ መራቢያ የሚሆኑ ቦታዎችን ከማጽዳት ጎን ለጎን የአልጋ አጎበር በአግባቡ በመጠቀም ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን ከበሽታው መከላከል እንደቻሉ የተናገሩት ደግሞ የአምቦ ከተማ ነዋሪ ሰናይት ታዬ ናቸው። የወባ ትንኝ እንዳይራባ አካባቢያቸውን የመጥረግና ያቆሩ ቦታዎችን የማዳፈን ሥራዎች በየሳምንቱ እያከናወኑ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ የእዚሁ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ባዩሽ ባልቻ ናቸው፡፡ ባለፈው ዓመት 484 ሺህ 150 የወባ ትንኝ መከላከያ የአልጋ አጎበር በዞኑ ወባማ አካባቢዎች ለሚገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎች መሰራጨቱን ከዞኑ ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት የተገኘ መረጃ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም